በአሜሪካ ምክር ቤት ምርጫ ዴሞክራቶች አብላጫ መቀመጫን አሸነፉ

በአሜሪካ አጋማሽ ምርጫ ዴሞክራቶች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላጫ መቀመጫን ማሸነፋቸው ተነግሯል።

ሪፐብሊካኖቹ በአንፃሩ የሴኔት መቀመጫዎችን ከመዳፋቸዉ ሳያስገቡ እንዳልቀረ  በመነገር ላይ ነዉ። ሆኖም የዴሞክራቶች የታችኛዉን ኮንግረስ አብላጫ ወንበር ማሸነፍ ለፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል ተብሏል።

በስምንት አመት ታሪክ ዉስጥ የአሜሪካ ዴሞክራቶች የታችኛውን የኮንግረስ ወንበር በአብላጫዉ መቆጣጠር መቻላቸዉ አሁን ፕሬዝደንት ትራምፕ የአሜሪካን ፖለቲካ እንዳሻቸዉ የሚያደርጉበትን ሥልጣን አጣብቂኝ ውስጥ መክተቱ አይቀሬ ነዉ ተብሏል።  

በተለይም ፕሬዝደንቱ በቀጣይ የያዟቸውን አጀንዳዎች እንዳያከናውኑ የማድረግ ሥልጣንም ሊኖራቸው እንደሚችልም ጭምር ነዉ የተነገረዉ።

ሆኖም የትራምፕ ፓርቲ አባላት የሆኑት ሪፐብሊካኖች ግን በሴኔቱ ያላቸዉን ስፍራ አጥናክረዋል ተብሏል። እናም የአሜሪካ የአጋማሽ ምርጫ ፕሬዝደንቱን የሚደግፉና የማይደግፉ አካላት የተለዩበት ነዉም ተብሏል። 

የዘንድሮዉ ምርጫ ልዩ ከሆነበት ምክንያቶች አንዱ የተመራጭ ሴቶች ቁጥር ከፍ ማለቱ ነዉ። ይህም በአሜሪካ ፖለቲካ የሴቶች አመት የሚል ስያሜም አሰጥቶታል የዘንድሮዉ ምርጫ።

ዴሞክራቶች ከዚህ ቀደም በፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ሲያሰሙት የነበረዉን ፀረ-ትራምፕ አቋም ከቃላት ተቃዉሞ አልፈዉ ዛሬ ላይ ትራምፕን አገኘንህ ያሉት ይመስላል።

ለዚህ ማሳያም የፓርቲዉ ሰዎች የፕሬዝደንቱን የሁለት አመታት የስልጣን ቆይታ በበጎ አልተመለከቱትምና ፊታቸዉን አዙረዉበታል። ይህንንም በአሁኑ ምርጫ በተግባር አሳይተዋል።

እናም ዴሞክራቶቹ የታችኛዉን የኮንግረስ ምርጫ በሰፊዉ ማሸነፋቸዉ በቀጣይ በፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ሊያነሱ የሚፈልገጓቸዉን ጥያቄዎች ሁሉ ህጉን ተከትለዉ እንዲያቀርቡ ያስችላቸዋል ተብሏል።

በዚህም የፕሬዝደንቱ የአስተዳደር ሥርዓት፣ የቢዝነስ ጉዳዮችና ከዚህ ቀደም ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸዉ በፊት የመንግስትን ግብር አጭበርብረዋል ሲባል የነበረዉንም ጉዳይ ጭምር ዴሞክራቶቹ በጥልቀት ይመረምራሉ ተብሎ ተጠብቋል።

ከዛም ባለፈ ፕሬዝደንት ትራምፕ ቀደምት የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች በብዙ ልፋት ጠንካራ መሰረት ላይ ያቆሙትን የዲፕሎማሲና የመልካም ግንኙነት ካብ ፕሬዝደንቱ ወደ ስልጣን በመጡ በሁለት አመታት ዉስጥ ገደል መክተታቸዉ ሌላዉ የዴሞክራቶችን ትኩረት ከሚስቡ ጉዳዮች አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በዚህም ዴሞክራቶቹ ትራምፕ በዘፈቀደ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያለዉን የረዥም ጊዜ ወዳጅነት ሲያበላሹ የመመልከት ሞራልም አይኖራቸዉም ተብሏል።

በተለይም ትራምፕ ኢራንና ሜክሲኮን ጨምሮ ከበርካታ ሀገራት ጋር ዉዝግብ ዉስጥ መግባታቸዉ ለዴሞክራቶቹ ተቀባይነት የለዉም። እናም ዴሞክራቶቹ የአሜሪካን የቀደመ መልካም ስም ለመመለስና ከሀገራት ጋርም ያለዉ ወዳጅነት እንዲቀጥል ለማስቻል ይሰራሉ ተብሏል።

ለአብነትም ትራምፕ በሜክሲኮ ድንበር ላይ የግንብ አጥር እንገነባለን የሚለዉ ሀሳባቸዉም ጭምር በዴሞክራቶቹ ውድቅ ሳይሆንባቸው እንደማይቀር በመነገር ላይ ነዉ።  

በምርጫው ያሸነፉ ሴቶች ቁጥር በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛው መሆንም ሌላው የዘንድሮውን ምርጫን ልዩ ካደረጉት ጉዳዮች ዋነኛው ነው። ለአብነትም የኒዉ ዮርኳ የዴምክራቶች እጩ የሆነችዉ ኦካሲዎ ኮርቴዝ ገና በ29 አመቷ የኮንግረስ አባል ለመሆን መመረጧ ሌላዉ ታሪክ ነዉ። በተለይም ኮርቴዝ በታሪክ ወጣቷ እንስት የኮንግረስ አባል መሆን መቻሏ አዲስ ክስተት ሆኗል።

ይህ በዚህ ሳይበቃ የሚኒሶታዋ ኢልሃን ኦኢማርና የሚቺጋኗ ራሺዳ ትላይብ የመጀመሪያዎቹ እንስት ሙስሊም የኮንግረስ አባላት መሆናቸዉም በአሜሪካ ፖለቲካ አሁን ላይ ሙስሊሞችም ቦታ እያገኙ መምጣታቸዉን ያመላክታል ተብሏል።

ሴት ዴሞክራቶች ለዚህ መብቃታቸዉ በአሜሪካ ፖለቲካ ተፅኖ መፍጠር የሚችሉት ሴቶች ቁጥር ከፍ እንዲል ያደርገዋል የተባለ ሲሆን ይህም በአሜሪካ ፖለቲካ በታሪክነት የሚሰፍር ነዉ ተብሏል።  

የካንሳሷ ሻሪስ ዴቪድስና የኒዉ ሜክሲኮዋ ዴብራ ሃላንድ የመጀመሪያዎቹ ተወላጅ የሀገሬዉ እንስት የኮንግረስ አባላት በመሆንም በታሪክን ተመዝግበዋል። አስገራሚዉ ጉዳይ ግን የካንሳሷ እጩ ሻሪስ ዴቪድስ ካንሳስን የወከለች የመጀመሪያዋ ሴት ግብረሰዶም ተወካይ ነች ተብሏል። አያና ፕሬስሌይ ደግሞ ቀዳሚዋ የማሳቹሴት ባለ ጥቁር ቆዳ እንስት ተመራጭ ሆናች።

ምንም እንኳን ዴሞክራቶች የታችኛዉን የኮንግረስ ወንበሮች በአብላጫ ቢቆጣጠሩትም ሪፐብሊካኖቹ በአንፃሩ የላይኛዉን የኮንግረስ ስፍራ ከመዳፋቸው ማስገባታቸው ተነግሯል።

በዚህም በላይኛው ኮንግረስ አባል የነበሩት ሶስት ዴሞክራቶች በሪፐሊካኖች መሸነፋቸዉ የላይኛዉ የኮንግረስ ስፍራ በሪፐብሊካኖች እጅ መዉደቁ እንደማይቀር አመላካች ነዉ አስብሏል። ከዛም በተጨማሪ የፍሎሪዳዉ የዴሞክራት ሰዉ ቢል ኔልሰንም ቢሆኑ በላይኛዉ ኮንግረስ አባልነታቸዉ የመቀጠላቸዉ ጉዳይ አጣራጣሪ ነዉ ተብሏል።

በ2016ቱ የአሜሪካ ምርጫ ብርቱ ተፎካካሪ የነበሩት ሪፐብሊካኑ ሴናተር ቴድ ክሩዝ ከወጣቱ የዴሞክራት ሰዉ ቤቶ ኦሮርክ ብርቱ ፉክክር ቢገጥባቸዉም ማሸነፍ መቻላቸዉ ተነግሯል።

ታዋቂ ፖለቲከኛና በ2012ቱ የአሜሪካ ምርጫ በባራክ ኦባማ ተሸንፈዉ የፕሬዝደንትነት ስፍራዉን ያጡት ሪፐብሊካኑ ሚት ሩምኒም በሴናተርነት የመቀጠል ጉዟቸዉን በስኬት መታጀቡ ተሰምቷል።

 ከእዉቋ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ቴይለር ስዊፍት ጋር የቴኔዝ ግዛትን በሴናተርነት ለመወከለ የተፎካከረችዉ ማርሻል ብላክበርንም አከባቢዉን በዚህ ደረጃ የወከለች ቀዳሚዋ እንስት ሆናለች።

አሁን በአሜሪካ ፖለቲካ እሆነ ያለዉ ነገር በብዙ ጉዳዮች ለየት ያለ ቢሆንም የሪፐብሊካኖች በኮንግረስ መሸነፍና የዴሞክራቶች ድል መቀዳጀት በአይነቱ የተለየ እንዳለሆነ ተነግሯል። ከዚህ ቀደም በነበሩት የምርጫ ጊዜያትም ቢሆን ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ በአዲሱ ፕሬዝደንት የመጀመሪያው አጋማሽ ምርጫ የኮንግረስን ድጋፍ የማግኘቱ እድል አናሳ ነበር ተብሏል።

አሁን ዴሞክራቶች በሴኔቱ ያላቸዉን ስፍራ ማጣታቸዉ ፕሬዝደንት ትራምፕን ጮቤ አስረግጧል። በተለይ ሪፐብሊካኖች የሴኔቱን ቦታ መቆጣጠራቸዉ በመጠኑም ቢሆን ትራምፕ እቅዳቸዉን ለማሳካት የሚያደርጉትን ጥረት ይረዳቸዋል ሲል ዘገበዉ ቢቢሲ ነዉ።