ሰሞኑን በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በሁለት ተማሪዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት የሶስት ተማሪዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ

ሰሞኑን በአሶሳ ዩንቨርሲቲ በሁለት ተማሪዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት በመስፋፋቱና መልኩን ወደ ብሔር  በመቀየሩ ምክንያት የሶስት ተማሪዎች ህይወት ማለፉ ተገልጿል፡፡

በህዳር 11፤ 2011 ዓ.ም በተፈጠረው በዚህ ግጭት ከ30 በላይ ተማሪዎች ለጉዳት መዳረጋቸውን የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማሪያም ለጋዜጠኞች በሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጸዋል፡፡

ከግጭቱ በስተጀርባ የፖለቲካ ሴራ ሊኖር እንደሚችልም ሚኒስትሯ ጠቁሟል፡፡

ሚኒስትሯ በመግለጫቸው መንግስት ግጭቱ ወደ ሌሎች ዩንቨርሲቲዎች እንዳይዛመትና የአሶሳ ዩኒቨርሲቲም ወደ ቀድሞ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲመለስ የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚሁም ከኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች፣ ከሳይንስ እና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ልዑክ በነገው እለት ወደ አሶሳ በማቅናት ውይይት እንደሚደረግ ዶክተር ሂሩት በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

ሚንስትሯ  በተጨማሪ ተማሪዎቹ በትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩና ለአፍራሽ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑም አሳስበዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሁሉንም ኢትዮጵያ ክፍሎችን የሚወክል ትውልድ የሚገኝባቸው በመሆኑ እርስ በርስ የመጠቃቃት፣ ያለመተማመንና የብሔር ጥላቻን ለማስፋፋት የሚያልሙ አፍራሽ ኃይሎችን በመከላከልና ጥንቃቄ በማድረግ ተቋማቱን የእውቀት መሸጋገሪያ ብቻ  እንዲሁም ማንነታቸውንና እትዮጵያዊነታቸውን የሚያዳብሩብት ቦታ በመሆኑ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ተናግረዋል፡፡