በሶማሌ ክልል የሕብረተሰቡን የልማት ችግሮች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ም/ር/መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሞሀመድ ገለጹ

በሶማሌ ክልል የሕብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሞሀመድ ገለጹ።

በሶማሌ ክልል የቆረሃይ ዞን የአገር ሽማግሌዎች፣ ጎሳ መሪዎችና የሕብረተሰብ ተወካዮች ከልማትና መልካም አስተዳደር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ከተመራው የልኡካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል።

በቆረሃይ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች እና ከቀብሪ ደሀር ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ባህላዊ መሪዎችና ነዋሪዎች በውይይት መድረኩ ላይ ሊፈቱ ይገባል ያሏቸውን ጥያቄዎች በመድረኩ ላይ አቅርበዋል።

የህብረተሰብ ተወካዮቹ ካነሷቸው የልማት ጥያቄዎች መካከል በዞኑ ከተሞችና ነዋሪዎች የሚስተዋለው የመጠጥ ውሃ ችግር፣ የመንገድና ጤና አገልግሎት እጥረት እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል አለመኖር በቀዳሚነት ተጠቃሽ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በአፋጣኝ እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ሙስጠፋ ሞሀመድ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ በክልሉ የሕብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የቀብሪ ደሀር ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት ዘንድሮ 200 ሚሊዮን ብር መመደቡንም በማሳያነት ገልጸዋል።

እንደ አቶ ሙስጠፋ ገለጻ የውሃ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከቀብሪ ደሃር ከተማ በተጨማሪ አራት የገጠር ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል።

ከመንገድ፣ ከጤና አገልግሎትና ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡ ያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎች ክልሉ ደረጃ በደረጃ እያየ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑንም አስረድተዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ በየጊዜው የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቀነስ ህብረተሰቡን ያሳተፉ ሥራዎች በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚከናወኑ አመልክተዋል።

የውሃ ፕሮጀክቱ በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት የቆረሃይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዲራህማን መሀመድ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ከ40 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ ከአገር ሽማግሌዎችና ጎሳ መሪዎች በተጨማሪ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ (ኢዜአ)