የዞን ምክር ቤቶች የሚያጸድቋቸው የክልልነት ጥያቄዎች ህገ-መንግስታዊ ቢሆኑም ከተቀመጡ አቅጣጫዎች ውጭ ናቸው—ደኢህዴን

በደቡብ ክልል የተለያዩ የዞን ምክር ቤቶች የሚያጸድቋቸው የክልልነት ጥያቄዎች ህገ-መንግስታዊ ቢሆኑም ከተቀመጡ አቅጣጫዎች ውጭ መሆናቸውን የደቡብ ኢትየጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ደኢህዴን ማእከላዊ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

በክልሉ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ድርጅቱ አቅጣጫ ማስቀመጡም ተገልጿል፡፡

የማዕከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ለሚዲዎች በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ባደረገው አጭር አስቸኳይ ጉባኤ በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከመከረ በኋላ የመፍትሔ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ድርጅቱ በ10ኛ መደበኛ ጉባኤው ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች ለማስፈጸምም “ከጉባኤው ማግስት ጀምሮ በተከናወኑ ተግባራት የመዋቅርና የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ለመፍታት ዝርዝር ጥናት ተከናውኗል” ብለዋል፡፡

በጥናቱ መሰረትም 44 ወረዳዎችና 3 ዞኖች መስፈርቱን በሟማላታቸው በአዲስ መልክ ተዋቅረው በክልሉ ምክር ቤት ጸድቆ ህጋዊ ማዕቀፍ እንዲይዙ መደረጉን ጠቅሰው በጥናቱ ተካተው ቀጣይ የህዝብ ውይይት የሚጠይቁና ውሳኔ ያልተሰጣቸው መኖራቸውንም አመልክተዋል።

“አደረጃጀት ልማትንና አገልግሎትን የሚያቀላጥፍ እንጂ በራሱ የልማት መጨረሻው ውጤት አይደለም” ያሉት አቶ ሞገስ ቀጣይ ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታትም የጥናት ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በተለያዩ አከባቢዎች የሚነሱና በምክር ቤቶች የሚፀድቁ ክልል የመሆን ጥያቄዎች ህገ-መንግስታዊ ቢሆኑም ደኢህዴን ካስቀመጠው አቅጣጫ ውጭ መሆናቸውን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

“ባለፉት 27 ዓመታት በአብሮነት በቆየንባቸው የልማት አቅሞችን ማስኬድ አስፈላጊ በመሆኑ የአደረጃጀት ጥያቄዎች ከፌደራል መንግስትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ምላሽ እንዲያገኙ ይሰራል” ብለዋል፡፡

የድርጅቱን 10ኛ ጉባኤ አቅጣጫዎችን በማክበር ውሳኔዎቹን ማስተላለፍ ተገቢ መሆኑን ገልጸው “ከአስተዳደራዊ መዋቅር ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ግጭቶች ለሰዎች ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት መሆን የለባቸውም” ብለዋል፡፡

በሸካ ዞን ቴፒና የኪ ወረዳዎች የተነሱ የመዋቅር ጥያቄዎች ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ተከትሎ የሚፈጸሙ ሆኖ ሳለ የመንግስት ተቋማትን በመዝጋትና አገልግሎት ማቋረጥ ተገቢነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

የአካባቢውን ሰላም ለማስመለስና ችግሩን ተነጋግሮ ለመፍታትም ጉዳዩን የሚከታተል ቡድን ወደ ስፍራው መላኩን ተናግረው በአካባቢው የሚገኙ የሰላም ኮሚቴዎች ለማረጋጋት ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል፡፡

ደኢህዴን ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር ሰላም እንዳይሰፍን በሚያደርጉ አካላት ላይ የህግ የበላይነት የማስከበር ስራ ለመስራትና ጠበቅ ያለ እርምጃ ለመውሰድ አቅጣጫ ማስቀመጡን አስረድተዋል።

ጥፋት የፈፀሙ ግለሰቦችን አጋልጦ በመስጠትና በማጋለጥ ሂደት ውስጥ ወጣቶች ምሁራን፣ የሀገር ሸማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በክልሉ አመራርን መልሶ የማደረጃት ስራ ህዝቡን በማስተቸት መከናወኑን የገለጹት ሃላፊው ለአዳዲሶቹ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመጪው ሳምንት እንደሚጀመሩ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶች በሃገሪቱ የተጀመረውን የለውጥና የመደመር ጉዞ ለማደናቀፍ በሚጥሩ ሃይሎች የሚመሩ መሆናቸው በተጨባጭ መረጃ መረጋገጡን ገልጸዋል፡፡ (ኢዜአ)