በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራና በትብብር መንፈስ መሥራት ይገባቸዋል – አቶ ለማ መገርሳ

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአገርና ለክልል ጥቅም በተባበረ መንፈስ በጋራ መስራት እንዳለባቸው  የኦዴፓ  ምክትል  ሊቀመንበር  አቶ ለማ መገርሳ  ተናገሩ ።      

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች  የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ የኦሮሞ ባህል ማዕከል አዳራሽ  የተጀመረ  ሲሆን በኦሮሚያ ክልል በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ 14 የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች  በመሳተፍ ላይ ናቸው ።

አቶ  ለማ በምክክር መድረኩ ላይ  እንደገለጹት የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ አንዱን በመረዳት እና በዘመናዊ የፖለቲካ መስመርን በመከተል  በሽግግር ወቅት ላይ እያገጠመ ያለውን አለመረጋጋት ለማለፍ  ይገባል ብለዋል።

በተለያዩ  ጊዜ  ጠላት በየእለቱ በሚሰጠን አጀንዳ ላይ እየተባላን ውለን እንድናድር እያደረገ ነው” ያሉት አቶ ለማ መገርሳ፥ ከውጭ ሆኖ እሳት እየወረወረብን ኦሮሚያን የብጥብጥ አውድማ ለማድረግ  የሚደረገውን ጥረት ማስቆም መቻል አለብን ብለዋል ።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ የኦሮሚያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለችግሩ መፍትሄ ከማበጀት ይልቅ ችግሩን የሚያባብሱ ተግባራትን ሲፈፅሙ እንደሚስተዋልም ነው አቶ ለማ የተናገሩት።

በዚህ መንገድ የሚመጣ ጉዳት የሁላችንም በመሆኑ ችግሩን አንድ ወገን ላይ ጥሎ ከመመልከት ይልቅ በተጠናከረ አንድነት ማለፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መስማማት ያስፈልጋል ብለዋል።

የኦዴፓ የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በመድረኩ ላይ የመነሻ ሀሳብ በማቅረብ በዚህም የኦሮሞ ህዝብ ትግል ከየት ወደየት በሚለው እና አሁን ባለበት ደረጃ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ አዲሱ የኦሮሞ ህዝብ ቀጣይ የትግል ምዕራፍ አቅጣጫ ዙሪያም በመነሻ ሓሳባቸው በማቅረብ በመድረኩ አብራርተዋል ።