ለውጡን ተከትሎ በአንዳንድ አካባቢዎች የታየው የሰላም መደፍረስ አገሪቱ ላይ ችግር እያስከተለ ነው–ወ/ሮ ሙፌሪያት ካሚል

የሰላም ሚኒስቴሯ ወይዘሮ ሙፌሪያት ካሚል ለውጡን ተከትሎ በአንዳንድ አካባቢዎች የታየው የሰላም መደፍረስ አገሪቱ ላይ ችግር እያስከተለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጸጥታ አካላት ሰላም ለማስከበርና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ማህበራዊ አቅሞችን ማዕከል ያደረገ ስራ ሊያከናውኑ እንደሚገባ ሚኒስትሯ አሳስበዋል።

ሚኒስቴሩ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የጸጥታ ኃላፊዎች ጋር በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት እያካሄደ ይገኛል፡፡

በውይይቱ ወቅት የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፌሪያት ካሚል በአንድ በኩል ለለውጥ በሌላ በኩል ለነውጥ ተጋላጭ መሆኑ ተፈጥሮአዊ ቢሆንም የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ አጠናክሮ በመቀጠል ሚዛኑ ለለውጥ ያደላ እንዲሆን በትጋት መሰራት ይገባል ብለዋል።

የሰላም ግንባታም ሆነ ሰላምን የማስከበር ስራ ለውጡን ከዳር ለማድረስ ሚናው የጎላ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ሙፌሪያት ህዝባዊ መሰረት ያላቸው የሰላም ግንባታዎችን ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዚህም የጸጥታ አካላት ህዝቡን ወደ ተረጋጋ ሁኔታ በመመለስ ‘የህዝብና የመንግስት አለኝታነታቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል’ ነው ያሉት።

በውይይቱ የሁሉም ክልሎች የጸጥታ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የፍትህ ቢሮ ኃላፊዎች ወቅታዊ ስራቸውን በተመለከተ ሪፖርት አቅርበዋል።