የቀድሞ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንደተዘጋ ማረጋገጡን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ

የቀድሞ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተዘግቶ ከቡራዩ የተፈናቀሉ ዜጎች በጊዜያዊነት እየኖሩበት መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማረጋገጡን አስታወቀ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በታህሳስ 3 ቀን 2011 ዓ.ም አደረኩት ባለው የመስክ ምልከታ ማዕከላዊ ስለመዘጋቱ እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሚገኙትን የህግ ታራሚዎች ተዟዙሮ መጎብኘቱን አመልክቷል፡፡

በቀድሞ የማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የተለያዩ ክፍሎች ከቡራዩ ከተማ የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች እየኖሩበት መሆኑን መመልከቱንም ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡

የክሊኒኩን ክፍሎችና የታራሚ ምግብ ማብሰያ ቤቱን የቋሚ ኮሚቴው አባላት ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን ለአንድ ታራሚ ብቻ ተፈቅደው የነበሩ ጠባብ ክፍሎች ክፍት መሆናቸውንም አስታውቋል፡፡

በምልከታውም ኮማንደር ኪዳኔ ማዕከላዊ ከመጋቢት 28 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ መዘጋቱንና በአሁኑ ሰዓት ምንም ታራሚ እንደሌለ ገልጸው 139 የፌዴራል ታራሚዎች ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማረሚያ ቤት በአደራ መልክ መዘዋወራቸውን ተናግረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሚገኙትን በህግ ጥላ ስር ያሉ ተጠርጣሪዎች ተዘዋውረው በጎበኙበት ወቅት ጀነራል ክንፈ ዳኘው፣ ኮሚሽነር ያሬድ ዘሪሁን፣ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ እና የቀድሞ የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ ሙሐመድ ዑመርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ታራሚዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደማይደርስባቸው እና የማረሚያ ቤቱ አያያዝና እንክብካቤ ጥሩ መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸውለታል፡፡

በሌላ በኩል በህግ ጥላ ስር ያሉ ተጠርጣሪዎቹ የፍትህ መጓተትና የክስ ሂደቱ ውስብስብ መሆኑን ገልጸው ሚዲያዎች ቀድመው ፍርድ እየሰጡ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

ሰሞኑን የተሰራጨው ዘጋቢ ፊልምም ፍርድ ቤት ውሣኔ ባልሰጠበት ክስ ላይ ትኩረት ማድረጉ ያሳደረብን የሞራል ተፅዕኖ ቀላል አይደለም ሲሉ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል፡፡ (ምንጭ፡-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት)