በኦሮሚያ ክልል የትጥቅ ትግል ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ መንገድ እየተመለሱ መሆኑ ተገለፀ

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የትጥቅ ትግል ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂ ሀይሎች መካከል በርከት ያሉት ወደ ሰላማዊ መንገድ እየተመለሱ መሆኑ ተገለፀ።

 የኦዲፒ የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ እንደገለፁት፥ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የትጥቅ ትግል ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች እንዳሉ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ ሰሞኑን የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች እና የፀጥታ አካላት እያደረጉ ባለው ጥረት በርከት ያሉ ታጣቂዎች በግል እና በቡድን በመሆን ሰላማዊ ትልግ ለማድረግ እና በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ያለውን ለውጥ ለመደገፍ ወስነው ወደ ሰላማዊ የትግል መስመር እየተመለሱ ይገኛሉ ብለዋል።

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ታጣቂዎች ሰላማዊ ትግል ለማድረግ በግል እና በቡድን እያሳለፉ ያለውን ውሳኔ እንደሚያበረታታም አቶ አዲሱ አስታውቀዋል።

ሰላማዊ ትግል ለማድረግ የወሰኑ ታጣቂዎችን በመቀበልም በፍላጎታቸው እና በችሎታቸው መሰረት በተለያየ የስራ መስክ ላይ እንዲሰማሩ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።

በተያያዘ ዜና በትናንትናው እለት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረ ጃርሶ ወረዳ በሞጎር በረሃ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 17 ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ትግል መመለሳቸው ተገልጿል።

 ታጣቂዎቹ ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመመለስ መወሰናቸውን ተከትሎም የወረ ጃርሶ ወረዳ አቀባበል እንዳደረገላቸው ታውቋል።