ምክር ቤቱ የአካባቢ ምርጫ ከቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ ጋር እንዲካሄድ ወሰነ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች ምክር ቤቶች ተወካዮች እንዲሁም የአካባቢ ምርጫ ከቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ ጋር እንዲካሄድ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አፅድቋል፡፡

ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን እያካሄደ ነው፡፡

በዚህም በ2011 ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች ምክር ቤቶች አባለት ምርጫና የአካባቢ ምርጫ በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ ማካሄድ ባለመቻሉ ከቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ ጋር እንዲካሄድ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አፅድቋል፡፡

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሃምሌ 4 ቀን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፃፈው ድብዳቤ፤ የሁለቱን ከተማ አስተዳደሮች ምክር ቤት ምርጫን በተቀመጠው ጊዜ ማለትም ዘንድሮም ማካሄድ አይቻልም ማለቱ ይታወሳል።

በቀረው አጭር የአመቱ ጊዜ ምርጫ አስፈፃሚዎችን መመልመል፣ ማደራጀትና ስልጠና ለመስጠት በቂ ጊዜ አለመኖሩን ቦርዱ በምክንያትነት አቅርቧል።

በዚህ ውሳኔ መስረትም አሁን በስራ ላይ ያሉት የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች በስራቸው ይቀጥላሉ።

ምክር ቤቱ በአስቸኳይ ስብሰባው የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባንክ ሥራ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጅን እየተመለከተ ይገኛል።

በተመሳሳይ የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጉምሩክ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ በመርመር ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡