2ኛው የዓለም አቀፍ የፖስታ አገልግሎት ህብረት ኮንግረስ ልዩ ስብሰባ በዛሬው ዕለት በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየተካሄደ ነው ።
የፖስታ ህብረት ኮንግረስ ልዩ ስብሰባው ከዛሬው ጀምሮ ለአምስት ቀናት ያህል የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል ።
ከ118 ዓመት በኋላ የዓለም አቀፍ የፖስታ አገልግሎት ህብረት ኮንግረስ በዛሬው ዕለት መካሄድ በተጀመረው ልዩ ስብሰባው የዓለም አቀፍ የፖስታ አገልግሎት ህብረት ጀነራል ዳይሬክተር በሽር አብዱራሂም ፣ ፕሬዚደንት ሙላቱ ና የኢፌዴሪ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚንስትር ወይዘሮ ኡባ መሐመድ ተገኝተዋል ።
ፕሬዚደንት ሙላቱ በስብሰባው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ጉባኤው በኢትዮጵያ በመካሄዱ ደስተኛ መሆናቸውንና የፖስታ አገልግሎትን ዘመናዊ በማድረግ ለዘላቂ ልማት የሚያበከክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል ።
የፖስታ አገልግሎቱን ዓለም አቀፍ አስተዋጽኦ ከፍ ለማድረግም በውይይቱ የሚሳተፉ የውሳኔ ሰጪዎች ሚናቸውን እንዲወጡ አደራ እላለው ብለዋል ።
የዓለም አቀፉ የፖስታ አገልግሎት ህብረት ጄነራል ዳይሬክተር በሽር አብዱራሂም በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የፖስታ አገልግሎትን ለማሳደግና አሠራሩን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የውይይት ነጥቦች ይነሳሉ ብለዋል ።
2ኛው ዓለም አቀፍ የፖስታ አገልግሎት ህብረት ኮንግረስ ልዩ ስብሰባም ስኬታማ እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ላደረገው አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል ።
የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ወይዘሮ ኡባ መሓመድ በበኩላቸው ዛሬ የተጀመረው ጉባኤው የፖስታ አገልግሎቱን ህልውና ለማስቀጠል ትኩረት በሚሠጥበት ጊዜ መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል ።
የፖስታ አገልግሎቱን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በመታገዝ ዘመናዊ የማድረግም ሥራዎችም እየተከናወኑ እንደሚገኝም ወይዘሮ ኡባ አያይዘው ገልጸዋል ።
የዓለም አቀፍ የፖስታ አገልግሎት ህብረት በአጠቃላይ 192 ያህል አባል አገራትን ያካተተ ሲሆን የመጀመሪያው ጉባኤው እኤአ በ1900 ነው የተካሄደው ።