ለትምህርት ጥራትና ተማሪዎች ውጤት መሻሻል የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

ለትምህርት ጥራት እና ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል የህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ ተገልጸዋል፡፡

በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን በ2010 ዓ.ም በ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የእውቅና እና የማበረታቻ ሽልማት የመስጠት ስነሥርዓት ተከናውኗል፡፡

በስልጤ ልማት ማህበር የተቋቋመው የሀይረንዚ ልዩ ሁለተኛና መሠናዶ ትምህርት ቤት በስምንተኛ ክፍል የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን አወዳድሮ በመቀበል የሚያስተምር ሲሆን በብሔራዊ ፈተና የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ በሀገር ደረጃ ተወዳዳሪ ተማሪዎች እያፈራ መሆኑ ተገልጸዋል፡፡

ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ አብዱልመጂድ ኑሬዲን በ2010 ዓ.ም ለፈተና ከተቀመጡ 82 የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል 70ዎቹ አራት ነጥብ ያስመዘገቡ ሲሆን ቀሪዎቹ ከ3 ነጥብ 5 በላይ ውጤት እንዳስመዘገቡ ተናግረዋል፡፡

በ12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና የተቀመጡ 98 ተማሪዎች በሙሉ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም እንደገቡና ከነዚህም ትምህርት ሚኒስትሩ ይፋ ባደረገው ድልድል 76 ተማሪዎች በህክምና ዘርፍ መግባታቸውን ርዕሰ መምህሩ አክለዋል፡፡

በስነሥርዓቱ ወቅት የትራንስፖርት ሚኒስትር አቶ ስራጅ ፈርጌሳ፣ አምባሳደር ረድዋን ሁሴን እና የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚገኙ የልማት ማህበሩ አባላትና የንግድ ማህበረሰብ የተገኙ ሲሆን በትምህርት ቤቱ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎችና ተማሪዎቹን ለዚህ ውጤት ላበቁ መምህራን የእውቅና እና ማበረታቻ ሽልማት ተደርጎላቸዋል፡፡

በስነሥርዓቱ ወቅት ንግር ያደረጉት የትራንስፖርት ሚኒስትር አቶ ስራጅ ፈርጌሳ የተመዘገበው ውጤት የሚያረካ ቢሆንም ሊያዘናጋ እንደማይገባ እና ተሸላሚ ተማሪዎችም ሳይዘናጉ ውጤታማነታቸውን በማስቀጠል የነገ ሀገር ተረካቢነት ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና 616 ነጥብ በማምጣት ከትምህርት ቤቱ አልፎ በክልል ደረጃ መጀመሪያ የሆነውን ውጤት በማስመዝገብ የዋንጫ፣ የወርቅ መዳሊያ፣ ላፕቶፕ እና የ10ሺህ ብር ተሸላሚ ወጣት አብዱልሰመድ አምዳ ትምህርት ቤቱ መምህራንና ሠራተኞች ያደረጉት እገዛ እና እርስበርስ ያዳበሩት መረዳዳት ለውጤት እንዳበቃቸው ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኙ የልማት ማህበር አባላትና የንግድ ማህበረሰብ አካላት ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ለተማሪዎቹ የገንዘብና የላፕቶፕ ኮምፒውተርን ጨምሮ የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶችን ለሽልማት ማቅረባቸው ተገልጸዋል፡፡

ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለገቡ ለነዚህ ተማሪዎች በየወሩ የ5 መቶ ብር ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸውም የልማት ማህበሩ አባላት ቃል ገብተዋል፡፡