የጂንካ ዩኒቨርስቲ በዘንድሮ ዓመት 1ሺ 500 ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረገ ነው

የጂንካ ዩኒቨርስቲ በ2011 ዓመት ምህረት 1ሺ 500 አዳዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ ።

የጂንካ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ገብሬ ሌንቲሶ ለዋልታ  እንደገለጹት  በዘንድሮ የበጀት  ዓመት የተማሪዎችን ቅበላ የተሳካ ለማድረግ በሁለት ዘርፍ የተከፈሉ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ ።

የኒቨርስቲው የዘንድሮ ዓመትን የመማርና  ማስተማር  ሂደቱን ለማስጀመር የመምህራን ዝግጅትን ጨምሮ የተማሪዎች የአገልግሎት መስጪያ ተቋማት የሆኑት ቤተ መጽሐፍትና የመመዝገቢያ  ሥፍራዎች በቴክኖሎጂ  የታገዙ እንዲሆኑ የማስቻል ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል ፕሬዚደንቱ ።

በጅንካ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች አገልግሎት መስጪያ ህንጻዎች ግንባታ መዘግየታቸውን  የገለጹት ፕሮፌሰር ገብሬ አዳዲስ ተማሪዎችን በጊዚያዊ የመጠሊያ ህንጻዎች እንዲገቡ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል ።

የጂንካ ዩኒቨርስቲ የዘንድሮ ዓመት  የተማሪዎች  የመግቢያ  ቀንም  እስካሁን  አለመቆረጡን  ፕሬዚደንቱ አያይዘው ገልጸዋል ።

የጂንካ ዩኒቨርስቲ  እስካሁን  ድረስ  በ14  የትምህርት ክፍሎችን በመክፈት  ተማሪዎችን  እያስተማረ መሆኑንና የኒቨርስቲው የትምህርት ክፍሎቹን  ወደ  41 ለማሳደግ  ዕቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑንም ፕሬዚደንቱ አብራርተዋል ።

አዳዲስ  የሚከፈቱት  የትምህርት  ዘርፎችም  በደቡብ ኦሞ ዞን  የሚታዩ የሙያ ክፍተቶችን ለመሙላት በሚያስችል መልኩ የሚከፈቱ  መሆኑም ተገልጿል።

የጂንካ ዩኒቨርስቲ ባለፈው ዓመት 1ሺህ 100 ያህል ተማሪዎችን የተቀበለ ሲሆን  በዘንድሮ ዓመት  1ሺ500 አዳዲስ ተማሪዎችን  በመቀበል  በአጠቃላይ ተማሪዎችን 2ሺህ 600 ለማድረስ እየሠራ ይገኛል ።

የጂንካ ዩኒቨርስቲ 2010 ዓም ከተከፈቱት 11 አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች አንዱ ነው ።