በሩሲያ ምስራቃዊ ክሬሚያ በደረሰ ፍንዳታ 18 ሰዎች ሲሞቱ ከአርባ በላይ ሰዎች ክፉኛ መጎዳታቸው ተገለጸ

በሩሲያ ምስራቃዊ ክሬሚያ በሚገኝ ኮሌጅ ላይ በደረሰ ፍንዳታ 18 ሰዎች ሲሞቱ ከአርባ በላይ ሰዎች ክፉኛ መጎዳታቸውን አንድ የክሬሚያ ከፍተኛ ባለስልጣን ተናግረዋል፡፡

የክሬሚያ ክልላዊ መሪ የሆኑት ሰርጌ አክሲኖቭ አደጋውን ያደረሰውን በአደጋው ህይወቱን ያጠፋው ወጣት የኮሌጁ ተማሪ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

የተማሪውን ስም ያልገለጹት መሪው ወጣቱ የአካባቢው ነዋሪ እንደነበርና አደጋውንም ያደረሰው ብቻውን ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጥቃቱ አሳዛኝ እንደነበር ጠቁመው ለተጎጂዎች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አክለውም የአደጋውን መንስኤ ለማጣራት ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
በአደጋው የተጎዱ ዜጎችም መንግስታቸው  አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል፡፡

የሩሲያ ከፍተኛ የምርመራ ድርጅት በኮሌጁ የደረሰው እልቂት በብረታ ብረት ቁርጥራጮች በተሞላ ፈንጂ መድረሱን ቢያስታውቅም የተለያዩ የሩሲያ የሚዲያ አውታሮች ግን ከማቿቹ ውስጥ ጥቂቶቹ ማንነቱ ባልታወቀ ግለሰብ በጠመንጃ ስለመገደላቸው ዘግበዋል፡፡

በኮሌጁ የደረሰው ፍንዳታ የሽብር ጥቃት ሊሆን እንደሚችል ዘገባው አመላክቷል፡፡ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ የሆኑት ዲሚትሪ ፔስኮቭ ባለስልጣናት የሽብር ጥቃቱን ያደረሰውን አካል በማፈላለግ ላይ መሆናቸውን ገልጸው ሌሎች ጉዳዮችን ከማብራራት ተቆጥበዋል፡፡
ጉዳዩን ተከትሎ የሩሲያ ብሄራዊ ጸረ-ሽብርተኝነት ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ በምስራቃዊ ክሬሚያ ከርች ከተማ በሚገኘው የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የደረሰው ፍንዳታ ምንነቱ ባልታወቀ የፍንዳታ መሳሪያ ምክንያት የተፈጠረ ስለመሆኑ አስታውቋል፡፡

ከኮሚቴው መግለጫ ቀደም ብሎ የአደጋ ጊዜ ሀላፊዎች እንደገለጹት አደጋው  የደረሰ በጋዝ ቆርቆሮ ፍንዳታ አማካኝነት ነው፡፡

የክሬሚያ አስተዳዳሪ ሰርጌ አክሲኖቭ እና የሩያ ጤና ሚኒስተር አደጋው ወደደረሰበት ቦታ ማቅናታቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡