ዩማን ብሪጅ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ለሻሸመኔ ሆስፒታል 60 በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አልጋዎች ከነፍራሾቻቸዉ አበረከተ

ዩማን ብሪጅ የተሰኘ የሲውድን ግብረ ሰናይ ድርጅት ለሻሸመኔ ሆስፒታል 60 በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አልጋዎች ከነፍራሾቻቸዉ አበርክተዋል፡፡

በታዳጊ ሀገራት ለሚገኑ የህክምና ተቋማት የህክምና መሳያዎችን ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የሚታወቀው ሂማን ብረጅ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት  በኢትዮጵያ  በፌደራል  እና በክልል ደረጃ በሚገኙ የህክምና ተቋማት  የተለያዩ የህክምና ማሳሪያዎችን ድጋፍ በማድረግ የሚታወቀው ሲሆን ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ 20 ሆስፒታሎች የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ 

በቀጣይም ለ100 ሆስፒታሎች በአምስት አመት ውስጥ ድጋፍ ለማድረግ በእቅድ መያዙ ነው የተገለጸው፡፡

በትላንትናው ዕለት የዚህ እቅድ አካል የሆነው የሻሸመኔ ሆስፒታልም በሆስፒታሉ ለረዥም ጊዜ እንደችግር ሲነሱ ከነበሩ ችግሮች መካከል ሆስፒታሉ የሚሰጠዉ አገልግሎትና ያሉት አልጋዎች ቁጥርና ጥራት አለመመጣጠን አንዱ ሲሆን፥ ይህንን ችግር በመጠኑ ሊቀርፍ የሚችል 60 በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አልጋዎች ከነፍራሾቻቸዉ ተበርክቶለታል።

በእለቱም የሆስፒታሉን የስራ እንቅስቃሴ የኢፌዴሪ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፤አምባሳደር መለስ አለም፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር  ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን፤ የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ደረጄ ዱጉማና ሌሎችም የፌዴራልና የኦሮሚያ የክልል የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች በጋራ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

በሆስፒታሉም ለረጀም ጊዜ ከአገልግሎት አሰጣጥና ከጥራት ጋር ተያይዞ ጥያቄ ሲነሳበት የነበረ ሆስፒታል መሆኑን ያስታወሱት የአካባቢው ነዋሪዎች የተለያዩ ጥያቄዎችም አንስተዋል፡፡

በተለይም አዲስ የተሰራው ሆስፒታል ህንፃው አልቆ አገልግሎት መስጠት ቢጀምርም የባለሙያ እና የህክምና ቁሳቁስ ባለመሙላቱ ሁሉንም አገልግልት ማግኘት እንዳልቻሉ እንስተዋል፡፡

በተያያዘም ከሆስፒታል ማስፋፋት ጋር ተያይዞ የህንፃ ስራዎች መጓተትም እንደችግር ተነስቷል፡፡

የሻሸመኔ ሪፌራል ሆስፒታል የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋትና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ያነሱት የኦሮሚያ ከልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን የክልሉ መንግስትም የሆስፒታሉ አንደኛዉ ችግር የሆነዉን የማስፋፊያ ግንባታ መጓተት ለመፍታት ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢፌዴሪ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ  በበኩላቸው ሆስፒታሉ ያለበትን የህክምና መስጫ መሳሪያዎችና ሌሎችንም ችግሮች ለመቅረፍ የፌዴራል መንግስት ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር አስፈላጊዉን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።