ጠ/ሚ አብይ አህመድ የ4 ቢሊየን ዛፍ ተከላ መርሃ ግብርን አስጀመሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ 4 ቢሊየን ዛፍ የሚተከልበትን ብሄራዊ የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም መርሃ ግብር ዛሬ ችግኝ በመትከል በይፋ አስጀምረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትርሩ መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት ከግብርና ትራንስፎርሜሽን አመራሮች ጋር በአዳማ ከተማ ውይይት ካካሄዱ በኋላ ነው።

በውይይቱም ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በመቀነሱ በዚህ መርሃ ግብር 40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ መልሶ ለመትከል መታቀዱን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በዚህ መሰረትም ዛሬ በይፋ በተጀመረው ብሄራዊ የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም መርሃ ግብር በቀጣዩ ክረምረት ወቅት በመላ ሀገሪቱ 4 ቢሊየን የሚሆኑ ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዟል።

የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በሀገር አቀፍ ደረጃ ብሄራዊ የደን ልማት ንቅናቄና የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እንደሚከናወን ማስታወቁ ይታወሳል።

ኮሚሽኑ በብሄራዊ ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራና የተለያዩ ዘርፎችን የሚመሩ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ዓላማውን በበላይነት እንዲመራ መመስረቱንም ተነግሯል።

የአረንጓዴ ልማት ንቅናቄው ዓላማም በችግኞች ፅድቀት ተግዳሮቶች ምክንያት የከሰሙና የቀጨጬ ችግኞችን በተሻሻለ ሁኔታ ለመተካት መሆኑ ተገልጿል።