የሃጅና ኡምራ ተጓዦች ያለእንግልት ደርሰው እንዲመለሱ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ

ለሃጅና ኡምራ የሚጓዙ ዜጎች ያለምንም ችግር ደርሰው እንዲመለሱ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ገለጸ፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ ከዚህ በፊት ለሃጅና ኡምራ ወደ ሳውዲ አረቢያ ሲሄድ የሚደርሰውን እንግልት ለመቀነስ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ኮሚቴ በማቋቋም ችግሩን እንዲቀል እያደረገ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው፡፡

በዚህም የአውሮፕላን ወጪን ጨምሮ እያንዳንዱ ተጓዥ 78 ሺህ 150 ብር መክፈል የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ገንዘቡን የሚከፍለው በባንክ ብቻ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ክፍያውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ እንዲሁም በኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ በተከፈቱ የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች የሚፈጸም እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ጉዞ የሚያደርግ ሰው ከሰኔ 1/2011 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በኩል ምዝገባ ማድረግ እንደሚችሉና ማሟላት ያለባቸውን ቅድመ ዝግጅቶች ማጠናቀቅ እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡

ትኬቱን በግል ገዝተው መሄድ የሚፈልጉ ተጓዦችንም ምክር ቤቱ እንደሚያስተናግድና የተጓዦቹ ትኬት መሄጃ ከአዲስ አበባ እስከ መዲና መመለሻው ደግሞ ከጅዳ እስከ አዲስ አበባ መሆን አለበት ተብሏል፡፡