በጀርመን መንግስት ድጋፍ የሚተገበረው የሰለጠነ የሰው ኃይል ለአፍሪካ ዘላቂ ልማት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

በጀርመን መንግስት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ የሚተገበረው የሰለጠነ የሰው ኃይል ለአፍሪካ ዘላቂ ልማት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ፡፡

ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በስምንት የአፍሪካ ሀገራት ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፣ በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ቫግነር በየዓመቱ ከ20 ሚሊየን በላይ ወጣቶች ወደ ስራ ቢሰማሩም 42 በመቶዎቹ ዕለታዊ ገቢያቸው ከ1 ነጥብ 9 ዶላር በታች ነው ብለዋል፡፡ ይህም በአፍሪካ ያለው የስራ ዕድል እና የምጣኔ ሃብት ዕድገት አለመመጣጠን ያመጣው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ክፍተቱን ለመድፈንም የግሉ ዘርፍ የተሳተፈበት የስልጠና ተግባር ለውጥ አምጥቷል ነው ያሉት አምባሳደሯ፡፡

በኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ ያሳተፈ የሙያ ስልጠና ላለፉት አስርት አመታት ተግባራዊ እየተደረገ መቆየቱም ተገልጿል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፈሰር ሂሩት ወልደማሪያም በፕሮጀክቱ ላይ ተወዳድሮ ያሸነፈ ተቋም የሶስት መቶ ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ እንደምደረግለት አስታውቀዋል፡፡

ፕሮጅክቱም ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል የስራ ዕድል የሚያስገኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የሰለጠነ የሰው ኃይል ለአፍሪካ ዘላቂ ልማት ፕሮጀክት በጀርመን የገንዘብና የሙያ ድጋፍ በወጣቶች የስራ ዕድል ላይ እና የሙያ ልማት ላይ የሚሰራ ፕሮግራም መሆኑም ተገልጿል፡፡