ምክር ቤቱ በቀጣይ የፓርላማውን አሰራር ሊያዘምኑ በሚችሉ ጉዳዮች ተስማማ

የህዝብ ተወካዮች ምር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ በኢትዮጵያ ከአየርላንድ አምባሳደር ሶኒያ ሃይላንድ ጋር ቀጣይ የፓርላማ አሰራር ሊያዘምኑ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማሙ።

የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ እንደተናገሩት፤ ስምምነቱ የተሻለ ተሞክሮ ያለቸውን አገራት በማሳተፍ ቀጣይ የፓርላማ ስራውን ለማዘመን እና ህዝቡ የሚፈልገውን የዳበረ የፖለቲካ ምህዳርን ለማሳለጥ በሚያግዙ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት የሚያስችል ነው።

ፓርላማው በሚሰራቸው በተለይ ህግን በማውጣት፣ በክትትልና ቁጥጥር ስራ እንዲሁም የህዝብ ውክልና ስራዎች ላይ ከዚህ ቀደም ሲከተላቸው የነበሩ አሰራሮች ያሉት እንደነበር ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት እየመጣ ካለው አጠቃላይ አገራዊ ለውጥ ጋር ለማስኬድ አዳዲስ ስራዎችን ማካተት አስፈላጊ በመሆኑ አሰራሩን ለማዘመን ከተለያዩ ዩኒቨርትሲዎችና ከባለሙያዎች የተወጣጣ ቡድን በማቋቋም ስራዎች እየተሰሩ ናቸው ብለዋል።

ለተጀመረው መዋቅራዊ ለውጥ የሚያስፈልጉ ጉዳዮች በጥናት ተለይተው ቋሚ ኮሚቴዎች ተወያይተውባቸው የዕቅድ መርሐ ግብር የወጣላቸው መሆኑን ገልጸው፤ ስራው የባለሙያዎችንና የሌሎች አገራትን ተሞክሮ እና የገንዘብ ድጋፍ የሚጠይቅ በመሆኑ ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ በተደረገው ጥሪ  በመጀመሪያ የአየርላን መንግስት ጥሪውን ተቀብሎ መምጣቱን ተናግረዋል።

በቀጣይ የሚደረገውን የገንዘብም ድጋፍም ሆነ የግብዓት አቅርቦት በዕቅድ የሚመራ መሆኑን ተናግረዋል።

የአየርላንድ አምባሳደር ሲኒያ ሃይላንድ በበኩላቸው፤ ዛሬ የተደረገው ስምምነት ውጤታማ የሆነ የፓርላማ ስርዓትን ለመገንባት ኢትዮጵያ ባደረገቸው ጥሪ መሰረት ነው።

ፓርላማው ባወጣው ፕሮግራም መሰረት የፓርላማውን አቅም ለማጎልበት ትኩረት በመስጠት በብቃት እንዲሰራ ለማድረግ የበኩላቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አምባሳደሯ ገልጸዋል።

አምባሳደሯ በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ እየመጣ ያለው የዴሞክራሲ ባህል መጐለበትና በሁሉም ዘርፍ እየታየ ያለው ለውጥ የፓርላማው ድርሻው የጎላ በመሆኑና ይህም ለድጋፍ እዳነሳሳቸው ገልጸዋል፡፡