ጠ/ሚ ዐቢይ ሐምሌ 22 በመላ ሀገሪቱ 200 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል በተያዘው መርሃ ግብር ዙሪያ መልዕክት አስተላለፉ

ለብዙ ዘመናት ከኢትዮጵያ ሰማይ ስር ሲስተጋባ የኖረውና ‹ለምለሟ ሀገሬ› የሚለው እድሜ ጠገብ ዜማ የልጆቻችን የዛሬ እውነታ የእኛ ደግሞ ከጆሯችን ሁሌም ያለ ቅርብ ትዝታ ነው፡፡

ትናንት እውነት እና ሀሴት የነበረው፤ ዛሬ ግን ምኩን እና ቁጭት ሆኖ የቀረው ዝማሬ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ኅሊና ውስጥ አብዝቶ ይመላለሳል፡፡

እውነት ነው ሀገራችን ለምለም ነበረች- ዛሬ ግን አይደለችም፤ ምክንያቱም አባቶቻችን ያቆዩልንን እኛም በተራችን ለልጀቻችን አላቆየንም- እናም ልምላሜዋን እና አረንጓዴ ውበቷን ከትዝታ ብቻ አወዳጅተን አደራችንን በልተናል፡፡

ዜማዎቻችን ብቻ ሳይሆኑ ተረቶቻችንም ሀገራችን በደን የተሞላች እንደነበረች ይነግሩናል፡፡ በተረቶቻችን ውስጥ የምናገኛቸውን ብዙዎቹን እንስሳት ዛሬ በአካባቢያችን አናገኛቸውም፡፡

በየቋንቋችን ስማቸው ብቻ የቀረው የዛፍ ዓይነቶች ሀገራችን ዓይነተ ብዙ ደን እንደነበራት ቋሚ ምስክሮች ናቸው፡፡

የዛፎች ጉዳይ ለእኛ የውበት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የህልውና ጉዳይ ነው፤ የእምነት ጉዳይ ነው፤ የባህ ልጉዳይ ነው፤ የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው፤ ዛፍ ማለት እኛ ነን- እኛ ማለት ያለ ዛፍ ምንም ነን፡፡

የበረሃማነት መስፋፋትና የአየር ንብረት መዛባት ያስከተለው ቀውስ ሀገራችንን አደጋ ላይ ከመጣል አልፎ የስሟ መገለጫ እስከመሆን ደርሷል፡፡

ባለፉት ዐርባ ዓመታት ብቻ እያሠለሰ የሚመታን ድርቅ በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል የምናደርገውን ትግል ተፈታትኖታል፤ ወገኖቻችንንም ከክብር ማማ አውርዶ የተረጅነት ወለል ላይ አስቀምጦብናል፡፡

የዝናብ ወቅቶቻችን እየተዛቡ፣ ለጎረቤት ይተርፉ የነበሩት ወንዞቻችን እየጎደሉ፤ ምንጮቻችን እየነጠፉ፤ ወይናደጋው በረሐ፣ ደጋው ቆላ እየሆነ የህልውና አደጋ ጋርጦብናል፡፡ የራሳችንን ህልውና በራሳችን ጥርስ ግጠነው- የነበረውን አፍርሰን እንዲያ ያልነበርን መስለናል፡፡

ከተሞቻችን በአንድ በኩል በኢንዱስትሪዎችና በተሽከርካሪዎች ጢስ ይበከላሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዛፎቻቸውን ጨርሰው ከአንድ ፀሐይ ቢሆኑም የሦስት ፀሐይ ያህል በገረረ ንዳድ ተንቀልቅለው ህያው በድኑን ያቃጥላሉ፡፡

ከተሞቻችን የከተማ መቃጠያ መሆናቸው ቀርቶ የከተማ መኖሪያ እንዲሆኑ ደናማ ከተሞች መሆን አለባቸው፡፡

ወገባችንን አሥረን የምንሠራቸው ግድቦች በደለል እየተሞሉና በውኃ እጥረት እየተመቱ ልፋታችንን መና እያስቀረነው ነው፡፡

እጃችንን በእጃችን እየበላን ጸጸት ቁጭታችን ብዙ ነው፡፡ ይህ ቁጭት እና መብሰክሰካችን
የይቻላል ስሜታችንን አቀጣጥሎ ወደ አረንጓዴ ሰገነታችን በሀይል ካንደረደረን እሰየው፤ ቁጭት ብቻ ከሆነ ግን ዋይታችንን የማይቋጭ ያው ከንቱ ቁጭት ብቻ ነው፡፡

ሐይቆቻችን የነበራቸውን ቦታ እየለቀቁ፣ አንዳንዶቹ ከነባር ይዞታቸው ሲሸሹ ሌሎቹ ጨርሰው እየደረቁ ነው፡፡

ሀዘናችን መሪር ሆኗል፡፡ ለነ ሀረማያ ያፈሰስነው እንባ ገና ከጉንጫችን ሳይደርቅ የሌሎች ሀይቅ ጅረቶቻችንም ህልውና ጉዳይም ለሌላ ሀዘን እያጨን ነጋችንን ጽልም አርጎታል፡፡

በዚህም የተነሣ በዓሣ ሀብታችን ላይ ፈተና እየተደቀነ ነው፡፡ በሐይቆቻችን ላይ ሠፍረው
ይኖሩ የነበሩት አዕዋፋት ሀገር ጥለው እየኮበለሉ በሐይቆች ውስጥ የሚኖሩ እንስሳትም ዘራቸው እየተመናመነ ነው፡፡

እንባችንን ከአይናችን ለመክላትና ዋይታችንን ወደ ዝማሬ ለመቀየር ማን ይምጣ? ለእኛ ህመም እና ስቃይ ማሻሪያው እና ፈውሱም ያለው እኛው እጅ ነው፡፡

ዓለም ያደነቃቸው ታላላቅ ቤተ እምነቶቻችን የተሠሩት ከሀገር በቀል ዛፎች በተገኙ እንጨቶች ነበር፡፡

በውስጣቸው የምናገኛቸው ቅርሶችና ንዋያተ ቅዱሳት የተዘጋጁት ከኢትዮጵያውያን እንጨቶች ነበር፡፡

ሥዕሎቻችን፣ ቅርፆቻችንና የወግ ዕቃዎቻችን በሙሉ የደኖቻችን ውጤቶች ነበሩ፡፡

ቀደምቶቻችን የተጠበቡባቸው ዓምዶችና ወጋግራዎች፣ በሮችና መስኮቶች፣ ጣራዎችና አቴናዎች የደኖቻችን ትሩፋቶች ነበሩ፡፡

ትውፊታዊ ክዋኔዎቻችን ደኖቻችንን አበክረው ይፈልጓቸዋል፡፡ አረንጓዴው አለማችን የሁሉ ነገራችን አልፋ እና ኦሜጋ ነው፡፡

ሰርግ ሀዘናችን- ስግደት ሶላታችን- ልደት ሞታችን- አምልኮ ከበሯችን ወግ እና ጨወታችን እንኳን ከዛፍ- ደኖቻችን ጋር እጅጉን ተሰናስሏል፡፡ ህይወታችን ከደኖቻችን ጋር የተያያዘ ነው፡፡

የደኖቻችን መመናመን በጎ ዕሴቶቻችን እንዲመናመኑ አድርጎብናል፡፡ ዕርቅ፣ ሸንጎ፣ ውይይት፣ ታሪክ ነገራ፣ በባህላችን ውስጥ የሚከወኑት በዋርካዎቻችን ሥር ነው፡፡

በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ እና ትውስታ ውስጥ አረንጓዴ ደኖቻችን የደግነት፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የህይወትእና የተስፋ ውካዮች ናቸው፡፡ በገጠሬው ሕይወትና በከተሜው ትዝታ ውስጥ የሚገኙት የዱር ፍሬዎች የባህላችን አካላት ነበሩ፡፡

ሌላው ቀርቶ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎቻችን እንኳን የሚዘጋጁት ከደን ውጤቶቻችን ነው፡፡ በባህላችን የአንድ ዋርካ መውደቅ የአንድ እንጨት መውደቅ ሳይሆን የአንድ ትልቅ ሰው፤ የአንድ ትልቅ ሽማግሌ መውደቅ ምልክት ነው፡፡

በሀገራችን ብዙ ወገኖቻችን ኑሯቸውን በደኖችና በደን ውጤቶች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የደን ፍሬዎችን ለቅመው፣ የደን ቅጠሎችን ሰብስበው፣ የደን ውጤቶችን ቆርጠው፣ የደን ውጤቶችን ወደ ልዩ ልዩ ዕቃዎች ቀይረው፣ በመሸጥ ኑሯቸውን የመሠረቱ ናቸው፡፡

የሀገሪቱ ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጮች በአንድም በሌላም መንገድ ከደን ውጤቶቻችን ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡

ደኖቻችንና የዱር እንስሶቻችን የቱሪዝም ገቢያችን መሠረቶች፣ የአይናችን ማረፊያ ጌጦች፣ የባህል- ወግ እና እምነታችንም መከሰቻ ናቸው፡፡

እነዚህን ሁሉ ስንመለከት ነው የዛፍ ጉዳይ ለእኛ የቅንጦት ጉዳይ የማይሆነው፡፡ ከዚህ በፊትም እንደምለው ይህች ሀገር ከአባቶቻችን የወረስናት ብቻ ሳትሆን ከልጆቻችንም የተዋስናት መሆኗንም ማሰብ ተገቢ ነው፡፡

እኛም በተራችን ለልጆቻችን ስናስረከባት ከነበረሀዋ፣ ከነንዳዷ፣ ከነ ድርቋ እና ከነደለሏ እንዳይሆን የቤት ስራችንን እንሰራ ዘንድ ይገባናል፡፡

ከልጆቻችን ነፍስ ላይ የነጠቅነውን በምቹ ሀገር የመኖር የህልውና መሰረት ሳንውል ሳናድር ከመመለስ እና ከመተካት የሞራል፣ የእምነት እና የሰብአዊነት ጽኑ ጥያቄ ጋር የተፋጠጥንበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡

የሀገራችንን የደን ሽፋን እንዲያገግም ማድረግ ህልውናችንን ማጽናት፣ እምነታችንን መጠበቅ፣ ባህላችንን ማበልጸግ፣ ኢኮኖሚያችንን ማዳበር ነው፡፡

አራት ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ስንነሣ ለህልውናችን፣ ለእምነታችን፣ ለባህላችንና ለኢኮኖሚያችን ስንል ታጥቀን መነሣታችንም ጭምር ነው፡፡

ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያሳየው ተነሣሽነት ይህን ዓላማ እንደተረዳው የሚያሳይ ነው፡፡

ይህንን ሀገራዊ ዓላማ ለማሳካት እስካሁን ባደረግነው አረንጓዴ አሻራን የማሳረፍ ርብርብ ቢልየኖች ችግኞችን ተክለናል፡፡

ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን በምናደርገው ብሔራዊ የችግኝ ተከላ ቀን 200 ሚሊየን ችግኞችን በአንድ ቀን በመትከል የዓለምን ክብረ ወሰን እንሰብረዋለን፡፡ የያዝነው ክረምት ከማለፉ በፊትም አራት ቢሊየን ችግኞችን ተክለን ግባችንን እንመታለን፡፡

ይህን ስኬት ለማምጣት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና የክልል አመራሮች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ በችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች የሚገኙ ሠራተኞች፣ የግብርና ባለሙያዎችና ምሁራን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ኮሜዲያን፣ የሚዲያ ኃላፊዎችና ጋዜጠኞች፣ ነጋዴዎችና ታላላቅ ኮርፖሬሽኖች፣ ወጣቶችና ሕጻናት፣ አጓጓዦችና የጉልበት ሠራተኞች ላደረጉት ምትክ የማይገኝለት አስተዋጽኦ በራሴና በኢፌዴሪ መንግሥት ስም ላመሰግን እወዳለሁ፡፡

ለአንድ ሃገር ጉዳይ፣ አንድ ሆነን በዓላማ ከተነሣን የሚሳነን ነገር እንደማይኖር የአረንጓዴ አሻራ ስኬታችን ምስክር ነው፡፡

ከደን የተራቆተችውን ሀገራችንን ለማልበስ እንደተነሣነው ሁሉ ከሰላም ከፍቅርና ከይቅርታ እየተራቆተች የመጣችውን ሀገራችንንም አንድ ሆነን ማልበስ አለብን፡፡

አራት ቢሊየን ዛፍ በአንድ ክረምት መትከል ከቻልን አራቱን አስፈላጊ ሀገራዊ ዕሴቶችን፡- ሰላምን፣ ይቅርታን፣ ፍቅርንና አንድነትን መትከልና ማሳደግ አያቅተንም፡፡ በፍጹም፡፡

በቀሪው ጊዜ የተከልናቸውን ችግኞች በመጠበቅ፣ በመንከባከብና ለፍሬ በማብቃት መትከል ብቻ ሳይሆን ማሳደግም እንደምንችል እናሳይ፡፡

ዛፍ ብሔር፣ ቋንቋ፣ እምነትና ርእዮተ ዓለም የለውም፡፡ ሁሉም ዛፍ የሁላችንም ነው፡፡ የሠራነው ሥራም ከእነዚህ ሁሉ በላይ ነው፡፡

ክብካቤና ጥበቃውም እነዚህን ልዩነቶች ሁሉ አልፎ ሊደረግ የሚገባው ነው፡፡

ሐምሌ 22 ቀን ሁላችንም ማልደን በመውጣት፣ ችግኞችንም በተገቢ መንገድ በመትከል፣ አረንጓዴ አሻራችንን እናሳርፍ፡፡ ነገንም ዛሬ እንትከል፡፡