ሆስፒታሉ 10ሺ ለሚሆኑ ዜጎች የሞራ ግርዶሽ የአይን ህክምና በነጻ ሊሰጥ መሆኑን አስታወቀ
የአለርት ሆስፒታል አልባሳር ኢንተርናሽናል ከተሰኘ ሳኡዲ በቀል በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር የፊታችን ሐምሌ 27 እና 28 የሞራ ግርዶሽ የአይን ህክምና በነጻ ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ።
የአለርት ሆስፒታል ከሚታወቅበት የቆዳ ህክምና ባሻገር ከተለያዩ አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በሚሰጣቸው የአይን ህክምናዎች ብዙዎችን ከአይነ ስውርነት መታደጉን የሆስፒታሉ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አለምሰገድ ጫኔ ለዋልታ ገልጸዋል፡፡፡
ሆስፒታሉ የፊታችን ቅዳሜና እሁድ አልባሳር ከተሰኘ አለም አቀፍ በጎ አድራጎት ድርጅትና በሳኡዲ ከሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር በመተባበር 10ሺ ለሚሆኑ ዜጎች የአይን ህክምና ለመስጠት ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
ህክምናው በሳኡዲ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት የተቸገሩ ዜጎቻቸውን ለመርዳት ባደረጉት ጥረት የተገኘ ድጋፍ መሆኑን የገለጹት አቶ አለምሰገድ፤ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በመረዳዳት ዜጎችን ማገዝ የሚችሉ መሆኑን አመልክተዋልል።
ህክምናው ለአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ ላሉ ነዋሪዎች የሚሰጥ ሲሆን፤ የአይን ችግር ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በተጠቀሰው ቀን ማንነታቸውን የሚያሳይ መታወቂያ በመያዝ ህክምናውን ማግኘት ይችላሉ ብለዋል።