በመዲናዋ 98 ሺ ለሚልቁ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ ነው

በአዲስ አበባ ከተማ በጎ ፈቃደኞች የማጠናከሪያ ትምህርትና በስፖርት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በስነ ጥበብ ዙሪያ ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን ከ98 ሺህ በላይ ለሆኑ ተማሪዎች እየሰጡ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮ የበጎ ፈቃድ ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ትዕዛዙ እንደገለጹት÷ በ114 ትምህርት ቤቶች ከ5ኛ ክፍል እስከ 10 ክፍል ላሉ 62 ሺህ 700 ተማሪዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል።

በተጨማሪም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በኪነ ጥበብ፣ በስፖርትና ኢትዮጵያዊነት ዙሪያም ለ36 ሺህ ተማሪዎች ለሁለት ወራት ስልጠና እየተሰጠ ነው።

ወጣቱ ትውልድ የኢትዮጵያ ታሪክና ባህላዊ እሴቶችን የሚያትቱ መፅሀፎችን ከማንበብ ይልቅ በማህበራዊ ሚዲያዎች ተጠምዶ የሚውል መሆኑን ዳይሬክተሩ አመልክተው ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚሰጠው ስልጠናም ወጣቱ በስሜት የሚነዳ ሳይሆን ምክንያታዊ ትውልድ ለመፍጠር እንደሚረዳ አመልክተዋል።

የበጎ ፈቃድ ትምህርትና ስልጠና ከሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች መካከልም ዳግማዊ ምኒልክ፣ ጥቁር አንበሳ፣ ኮከበ ጽባህ እንደሚገኙባቸው ጠቅሰዋል።

ትምህርቱ እስከ ነሀሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የሚሰጥ መሆኑ መገለፁን የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅ ዘገባ ያመለክታል፡፡