ደስታ መሰል የእንሰሳት በሽታን እ.ኤ.አ እስከ 2027 ለማጥፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ኢትዮጵያ በጎችና ፍየሎችን የሚያጠቃዉን ደስታ መሰል የእንሰሳት በሽታ እ.ኤ.አ በ2027 ለማጥፋት እቅድ አዉጥታ እየሰራች መሆኗን አስታወቀች፡፡

የግብርና ሚኒስቴር እንደገለፀዉ እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ በ2011 ዓ.ም በ72 ሚሊዮን ብር በጀት ድንበር ዘለል የእንሰሳት በሽታን ለማጥፋት ነጻ የክትባት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ የበሽታዉን መድሀኒትም በሀገር ዉስጥ እየተመረተ ነው፡፡

ይህ ደስታ መስል የበጎችና ፍየሎች በሽታ ከእንሰሳት ወደ እንሰሳት በቫይረስ የሚተላለፍ ሲሆን በሰዉ ላይ የሚያደርሰዉ ጉዳት እንደሌለ ተገልጿል፡፡

ሀገሪቱ ከእንሰሳት ሀብት ሽያጭ የምታገኘዉ የዉጭ ገቢ ላይ በሽታዉ ተፅዕኖ እንደሚኖረዉ ተነግሯል፡፡

የአዉሮፓ ህብረትንና የአለም የምግብ ድርጅትን የመሳሰሉ መንግታዊ ያልሆኑ አለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ በሽታዉን ለማጥፋት የምታደርገዉን ጥረት እየደገፉ ይገኛሉ፡፡

ደስታ መሰል የበጎችና ፍየሎች በሽታን ለማጥፋት ቁጥጥር የሚያደርግ ፕሮጀክት እ.ኤ.አ ከ2016 ጀምሮ ሲተገበር ቆይቷል፡፡ በፕሮጀክቱ የተከናወኑ ስራዎችን የሚያሳይ የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡