ጠ/ሚ ዐቢይ በ2019 የሔስያን የሰላም ሽልማት ያገኙትን 25 ሺህ ዩሮ ለመልካም ወጣት ማዕከል ግንባታ አበረከቱ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከአውሮፓውያኑ የ2019 የሔስያን የሰላም ሽልማት ያገኙትን 25 ሺህ ዩሮ ለመልካም ወጣት ማዕከል ግንባታ አበረከቱ።

ለሰባት ተከታታይ ዙር በዚህ ክረምት በሃዋሳ በአገልጋይ እና በመልካም ወጣት ፕሮጀክት መሪ ዮናታን አክሊሉ አስተባባሪነት ሲካሄድ የነበረው መርሃ ግብር የመዝጊያ ስነ ስርዓት በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዝግጅቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት መልካም ወጣት ማለት ከማስመሰል ወደ መምሰል የሚያድግ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ማለት ወደ እውቀት፣ ጥበብና ፍቅር ወደ መስጠት ማደግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሱስ ሀሺሽ ብቻ አደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ዘርን ከዘር እና ሀይማኖትን ከሃይማኖት ማባላትም ሱስ ነው ብለዋል።

የውሸት፣ የዘረኝነት እና የዳተኝነት ብዙ ሱሰኛ ባሉበት ሀገር እናንተ ለማስተማሪያነት ተመርጣችኋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያውያን ክብር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አሁን የፖለቲካ እና የዘር አጀንዳችን መጠቀሚያ እያደረግናት ነው ብለዋል።

የፕሮቴስታንት አምነት ተከታዮች የኦሮቶዶክስ ሀይማኖትን ማክበር እና መውደድ የምርጫ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ግዴታችሁም ነው ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ቤተክርስቲያኗ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ አሻራ ማስቀመጧን በማንሳት፥ ቤተክርስቲያኗ ከእነ ክብሯ እንድትቀጥል እንፈልጋለን ነው ያሉት።

ሲያጠቃልሉም መልካም ወጣቶችም ሆኑ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ ካሉበት የከፍታ ስፍራ እንዳይለቁ አሳስበዋል።

የመልካም ወጣት ማዕከል ግንባታ ሀሳብ እንዳስደሰታቸው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በቅርቡ ኬሔስያን የሰላም ሽልማት ያገኙትን 25 ሺህ ዩሮ ለማዕከሉ ግንባታ እንዲውል አበርክተዋል።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው እንዲህ ዓይነቱ በራስ ተነሳሽነት የነገን ባለ ተስፋዎች እና የሀገር ሀብት የሆኑትን ወጣቶች በማሰባሰብ ከወራት በላይ በጎ መምከር እና በጎ ማስታጠቅ በፈጣሪም በፅድቅ ትልቅ ቦታ እንዳለው እና ለሀገርም ትልቅ ታሪክ ሰሪነት መሆኑን ገልጸዋል።

ሁሉም በየደረጃው በዚህ በመቅናት እና በመመኘት የራሱን ታሪክ መስራት እንዳለበትም አንስተዋል።

እንዲህ ይቅርታና ፍቅርን የሚያስተምሩ ሺዎች ከተሰለፉ ወደ ሚሊዮኖች አድገን በአጭር ጊዜ ራዕያችንን እናሳካለን ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

2009 ዓመተ ምህረት ላይ በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በየክረምቱ ሲከናወን ቆይቷል።