የሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የፖለቲካ እና ደህንነት ኮሚቴ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አተገባበር በተመለከተ በአዲስ አበባ ተገናኝተው ሊመክሩ ነው፡፡
ሁለቱ ሱዳኖች እንደ አዉሮፓዊያን የዘመን አቆጣጠር በ2012 የጋራ ስምምነት ተፈራሙ፡፡
ይህም ስምምነት የዜጎች መብት፣ የነዳጅ ጉዳይ፣ አጠቃላይ የቀጠናዉን ደህንነት እና የሁለቱ ሀገራት የገንዘብ አጠቃቀም እና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮችን ያጠቃለለ ነው፡፡
በ2013 ስምምነቱ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላቸዉን ስምምነት ቢያደርጉም በእቅዱ መሰረት ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም ነበር፡፡
በፈረንጆቹ 2011 ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን መቀዳጀቷን ተከትሎ የተፈጠረው አለመረጋጋት እና ሌሎችም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ስምምንቱን በእቅዱ መሰረት እንዳይተገበር ማድረጋቸውም ተነግሯል፡፡
በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍና ሃገራቱ የደረሱበትን ስምምነት ለመተግበር እና ስምምነታቸውን ለማደስ የሚያስችል ውይይት ለማድረግ የፊታችን ጥር 25 በአዲስ አበባ እንደሚገናኙ መቀማጫዉን ካርቱም ያደረገው የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤት አስታወቋል፡፡
ደቡብ ሱዳን ራሷን ችላ ከተገነጠለች በኋላ ሁለቱ ሀገራት በርካታ ጊዜያቸዉን እርስ በእርስ ሲካሰሱ እንዳጠፉ ያስታወሰው ዘገባው ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለዉን ግንኙነት እንዲሻክር አድርጎታል፡፡
በታቦ ሚምቤኪ ይመራ የነበረው የአፍሪካ ህብረት ቡድን ሀገራቱን ሲያሸማግል የቆየ ሲሆን አሁን ሁለቱ ሀገራት ሁለንተናዊ ጥቅማቸዉን ሊያስጠብቅ የሚያስችለዉን ስምምነት ተግባራዊ ሊያደርጉ የሚችሉበትን ጉዳይ ለመቋጨት አዲስ አበባ ተቀጣጥረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የደቡብ ሱዳን ህዝቦች በባለፈው ዓመት የሰበሰቡትን እህል ያክል ዘንድሮ ማማረት ባለመቻላቸው አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲል የዓለም አቀፉ የምግብ ተራድኦ አስታዉቋል፡፡
ደቡብ ሱዳን ወደ ግጭት ከገባች እ.ኤ.አ. ከ2013 በኋላ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿ ከቤት ንብረታቸው በመፈናቀላቸው በ2016 ከተሰበሰበው ምርት የ2017ቱ እጅግ አነስተኛ መሆኑን ነው ድርጅቱ ይፋ ያደረገው፡፡ ለእነዚህ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ካልተደረገላቸው በአሳሳቢ ደረጃ ውስጥ ይገኛሉ ሲል አስታቋል፡፡
በ2016 በአካባቢው ላይ በተፈጠረው የእርስ በርስ ግጭት ምክኒያት ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸዉን ያስታወሰው የተራድኦ ድርጅት አሁን ግን ከ6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ማለቱን ሱዳን ትሩቡን አስነብቧል