አሜሪካ ለፍልስጤም ስደተኞች ማህበር የምታደርገውን ድጋፍ ለመቀነስ ከውሳኔ መድረሷ ያሳስበኛል-የተባበሩት መንግስታት ድርጅት

አሜሪካ ለፍልስጤማዊያን ስደተኞች ማህበር የሚታደርገውን ድጋፍ ለመቀነስ ከውሳኔ ላይ መድረሷ እንደሚያሳስበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቋል፡፡

በፈረንጆቹ 2016 ብቻ አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ስደተኞችን መልሶ ለማቋቋም 368 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች፡፡

ይህም የመንግስታቱ ደርጅት በአካባቢው ለሚያከናውነው ሰብአዊ ተግባር ከሚያስፈልገው አጠቃላይ የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ 30 ከመቶውን ድርሻ ይይዛል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ እንዳሉት የአሜሪካ ውሳኔ እውን የሚሆን ከሆነ ድርጅቱ በጤና፣ ትምህርት እና ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ የነበረው ተሳትፎ ሊቀንስ ይችላል፡፡

ይህ ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን ክብር እና ደህንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ የሚያስገድድ ነው ብለዋል ዋና ጸሃፊው፡፡

የአሜሪካ መንግስት ቃል አቀባይ ሂዘር ናዌርት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የትራምፕ አስተዳደር በ2018 ዓ.ም ለፍልስጤማዊያን ስደተኞች የሚደረገውን ድጋፍ ከ125 ሚሊዮን ዶላር ወደ 60 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ መደረጉን ገልጸው ሌላው በሂደት የሚታይ ነው ብለዋል፡፡

የፍልስጤም ነጻ አውጪ ድርጅት አሜሪካ ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ የፍልስጤም ዜጎችን ለመጉዳት አነጣጥራለች ሲል ወቀሳ አቅርቧል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአንድ ወር በፊት ፍልስጤም ከእስራኤል ጋር ለመስማማት ባለመቻሏ የገንዘብ ድጋፋችንን ለመቀነስ እንገደዳለን ማለታቸው ይታወሳል፡፡

የፊሊስጤም ፕሬዝዳንት ማሃሙድ አባስ በበኩላቸው እሁድ እለት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ላይ የሰላ ትችት በማቅረብ አሜሪካ ያለችበት የትኛውንም ድርድርን እንደማይቀበሉ ማስታወቃቸው የቅርብ ትዝታ ነው፡፡