ሶማሊያ ከአውሮፓ ኮሚሽን የ100 ሚሊዬን ዩሮ የበጀት ድጋፍ ሊደረግላት ነው

የአውሮፓ ኮሚሽን ለሶማሊያ መንግስት በሀገሪቱ የተጀመሩ ማሻሻያዎችን ለማበረታታት የ100 ሚሊዮን ዮሮ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የአውሮፓ ኮሚሽን በሚቀጥለው ሁለት አመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ነው ለሶማሊያ የ100 ሚሊዬን ዩሮ የበጀት ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገባው የአገሪቱ መንግሥት እየተከተለች ያለውን ማሻሻያዎች ለመደገፍና የመንግሥት ተቋማትን ለማጠናከር በማሰብ ነው ።   

ከዚህ ባሻገር ድጋፉ በሀገሪቱ የተደቀኑ የኢኮኖሚ ስጋቶችን ለመመከት እና የተለያዩ አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ነው የተባለው፡፡

ድጋፉ የሶማሊያ መንግስት የተዋሃደች ፌደራላዊ ሀገርን እንዲገነባ ለማድረግ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተጠቁሟል፡፡

የበጀት ድጋፍ የሶማሊያ መንግስት በሀገሪቱ እየተከናወኑ የሚገኙ ማሻያያዎችን እንዲያቀላጥፍ ከማስቻሉም ባለፈ ለዜጎቹ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማቅረብ የምትችል ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት ያግዘዋል ሲሉ የሚናገሩት በዓለም አቀፍ ትብብር እና ልማት ማህበር የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽነር ኔቨን ሚሚካ ናቸው፡፡

የበጀት ድጋፉን በተመለከተ የሶማሊያው ጠቅላይ ሚንስትር ሀሰን አሊ ካይር በዓለም አቀፉ የትብብርና ልማት ማህበር የአውሮፓ ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር  ስቴፋኖ ማንሴርቪሲ ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ 

ሶማሊያ ለአመታት በጽንፈኛ አክራሪ ቡድኖች ስትታመስ የሰነበተች ሲሆን ይህም   በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ለሞት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ደግሞ ለስደት ተዳርገዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አለመረጋጋቱ የአገሪቷን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ማዳከሙም አይዘነጋም፡፡

የአልቀይዳ ቀኝ ክንፍ የሆነው  አልሻባብ የአፍሪካ ቀንዷን ሀገር መንግስት በመገልበጥ የራሱን እስላማዊ አገዛዝ ለመመሥረት ከፍተኛ ፍላጎት በማንገብ በሀገሪቷ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶችን ሲሰነዝር እንደነበር ይታወቃል፡፡

በሀገሪቱ የሚገኙ ታጣቂዎችን በማስወጣት በአንጻሩ መረጋጋትን ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የአፍሪካ ሀገራት እና ከአለም አቀፍ ሰላም አስከባሪ ኃይሎች በሶማሊያ አሁንም ድረስ  ሠፍረው ይገኛሉ፡፡  

ሶማሊያ ላለፉት ሶስት አሥርተ ዓመታት ገደማ ያለፈችበት አለመረጋጋት በየአመቱ ሄድ መለስ ከሚለው ድርቅ ጋር ተዳምሮ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ህዝቧን ለአስከፊ ድህነት መዳረጉን  ሲል ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡

አሁን ሶማሊያ ከአውሮፓ ኮሚሽን ያገኘችው የበጀት ድጋፍ የሀገሪቷ የግብርና ዘርፏን እንዲያንሰራራ እና የመሰረታዊ አገልግሎቶች አቆርቦት እንዲጠናከር የራሱን ድርሻ ይጫወታል ተብሎ ተስፋ ተጥሏል፡፡(ምንጭ: ሲጂቲኤን)