በጦላይ ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ ወጣቶች በያዝነው ሳምንት ይለቀቃሉ ተባለ

በአዲስ አበባ ከጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ሥር ውለው በጦላይ ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ ወጣቶች በያዝነው ሳምንት እንደሚለቀቁ ተገለፀ።

ወጣቶቹ ከመስከረም 2 እስከ መስከረም 8 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ከነበረው የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ነበር በቁጥጥር ስር የዋሉት።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ ጀማል እንደተናገሩት፥ በመንግስት በኩል በቁጥጥር ስር ለዋሉት ወጣቶቹ እስካሁን የተለያዩ ስልጠናዎችን ሲወስዱ ቆይተዋል።

በጦላይ ለአንድ ወር እራስን ከወንጀል ስለማራቅ እና ተያያዠ ስልጠናዎችን ለመስጠት የተያዘው የጊዜ ሰሌዳም የፊታችን ሀሙስ ይጠናቀቃል ብለዋል ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ ጀማል።

አስፈላጊው ሎጀስቲክስ ሚሟላ ከሆነ ወጣቶቹ የፊታችን ሀሙስ ካልሆነ ደግሞ እስከ መጪው ቅዳሜ ድረስ የሚለቀቁ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ዘይኑ ወጣቶችን አስተምሮ ከመልቀቅ ባለፈ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ስራ አጥ የሆኑትን በጥቃቅንና አነስተኛ አደራጅቶ ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።

በከተማዋ በነበረው የጸጥታ ችግር በቁጥጥር ስር ውለው ስልጠና ሲከታተሉ የነበሩ 1 ሺ 204 ወጣቶች ሲሆኑ፥ ከነዚህ ውስጥ በወንጀል የተጠረጠሩት 83 ወጣቶች በህግ የሚጠየቁ ናቸው ብለዋል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)