ሶማሊያ በሀገሯ የሚገኙትን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ ባለስልጣን ሀገሯን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች

ሶማሊያ በሀገሯ የሚገኙትን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ ባለስልጣን ሀገሯን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች

የሶማሊያ መንግስት ትዕዛዙን ያስተላለፈው ባለስልጣኑ በብሄራዊ ሉአላዊነቴ ጣልቃ ገብቷል በሚል ነው፡፡

የአልቀይዳ ቀኝ ክንፍ የሆነው አልሸባብ በሚያደርሳቸው ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶች የምትናጠው ሶማሊያ  ከባድ የተባለ ውሳኔ አስተላለፈች፡፡

የሶማሊያ መንግስት ብሄራዊ ሉአላዊነቴን ተፈታትነዋል ያላቸውን የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ባለስልጣን በአስቸኳይ ሀገሬን ለቀው እንዲወጡ ሲል ትዕዛዝ ማስተላለፉ ተሰምቷል፡፡

የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ያወጣው መግለጫ በሶማሊያ የሚገኙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና መልዕክተኛ ኒኮላስ ሀይሶም ከዚህ በኋላ የመንግስታቱን ድርጅት በሀገሪቱ እንደማይወክሉና ምንም አይነት ስራ ሊሰሩ እንደማይችሉ ያመላክታል፡፡

የአፍሪካ ቀንዷ ሀገር ባሳለፈችው በዚህ ውሳኔ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እስካሁን የሠጠው ምንም አይነት ምላሽ የለም፡፡  

እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ 1991 በሶማሊያ የነበሩ የጎሳ መሪዎች በወቅቱ የነበረውን አምባገነን አገዛዝ ካስወገዱ በኋላ እርስ በርስ በመጋጨታቸው ሳቢያ የተነሳውን የእርስ በእርስ ጦርነት ለመቅረፍ በተደረገው ጥረት የመንግስታቱ ድርጅት ዋነኛ ድጋፍ ሰጪ አካል ነው፡፡

የአልሸባብ የቀድሞው ታጣቂ የነበሩትና በ2017 በይፋ ህዝቡን ይቅርታ ጠይቀው የኋላ ኋላ የክልል አስተዳዳሪ ለመሆን የሚያስችላቸውን የምርጫ ውጤት ያሸነፉት ሙክታር ሮቦው በቁጥጥር ስራ መዋላቸውን ተከትሎ ሀይሶም ለሶማሊያ ሀገር ውስጥ ሚንስቴር በጻፉት ደብዳቤ ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸው የሶማሊያ መንግስት ጥርስ ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸው ጉዳይ ነው፡፡

በተጨማሪም ሙክታር ሮቦ በታሠሩበት ጊዜ ባይደዋ ውስጥ በተደረገ ሠላማዊ ሰልፍ የደረሰውን እልቂትና እሥራት ለመመርመር መንግስት ምን አይነት እርምጃ እንደወሰደ መጠየቃቸውም በምክንያትነት ይጠቀሳል ፡፡

ከዚህም ባለፈ ኒኮላስ ሀይሶም ከሀገሪቱ እንዲወጡ ትዕዛዝ የተላለፈባቸው በመንግስታቱ ድርጅት የሚደገፈው የሶማሊያ የፀጥታ ሀይል በዚሁ በሮቦ ቁጥጥር ስራ መዋል እጁ ሳይኖርበት አይቀርም የሚል ሪፖርት በማቅረባቸው ነው፡፡  

የሶማሊያን ማዕከላዊ መንግስት በማፍረስ የራሱን እስላማዊ አገዛዝ ለመመስርት ከአስረተ አመታት በላይ ጥረት ሲያደርግ የቆየው አልሸባብ እ.ኤ.አ. በ 2011 ከዋና ከተማው ሞቃዲሾ የተወገደ ቢሆንም በደቡብ ምዕራብ ክልል ጨምሮ በሌሎችም ግዛቶች ላይ ስጋት መሆኑን ዛሬም አላቆመም።(ምንጭ:  የሮይተርሱ )