የእንግሊዝ እና የጀርመን የንግድ ምክር ቤቶች እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት ስትወጣ የጋራ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ቅድሚያ ሠጥተው መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
የብሪታንያ እና የጀርመን የንግድ ምክር ቤቶች በውይይታቸው እንደገለፁት ከሆነ በንግድ ዘርፍ የሚስተዋሉ የኢኮኖሚ አለመረጋጋትን ሊያከትሉ የሚችሉ ችግሮችን ለመቀነስ በሰራተኞች መብት፣ በግብር እና በግምሩክ አሠራር ሂደት ላይ ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
የጀርመን የንግድ ምክር ቤት አባላት ከእንግሊዝ ጋር እየተደረገ ያለው የንግድ ልውውጥ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሆነ የገለፁ ሲሆን የእንግሊዝ የንግድ ምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ተፈጥሯል የተባለውን የኢኮኖሚ ችግር ለማቃለል ቢያንስ ሶስት የሽግግር ዓመታት እንደሚያስፈልጋቸው ገልፀዋል፡፡
የእንግሊዝ የንግድ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አደም ማርሻል እንደገለጹት "በሁለቱም ሃገራት መህል እውነተኛ የንግድ ሥራ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ስራ ለመስራት እለት ተእለት በንግድ ሥራ ላይ ያሉ ማነቆዎችን በመለየት እና የወደፊቱን የግብይት አሠራር ሂደት በማጥራት ግልጽነት ያለው አሰራር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡
የሁለቱም ሃገራት ድርጅቶች በኢንቨስትመንት ጉዳዮች ዙሪያ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ውሳኔዎችን መወሰን የሚችሉበትን መንገድ ለመፍጠር እንግሊዝ እና የአውሮፓ ህብረት በጉምሩክ ስርዓት ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸውም ተገልጿል፡፡
የእንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት መውጣት የንግድ ትስስሩ ላይ አሉታዊ ጫና በመፍጠር ተጨማሪ ቢሮክራሲ እና ጥብቅ የሆነ የድንበር ቁጥጥር በመፍጠሩ የጀርመን ድርጅቶች ከፍተኛ ወጪ እንዲያወጡ በመገደድ ላይ ናቸው ሲሉ የጀርመን የንግድ ምክር ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ማርቲን ዋንስሌበን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ አባላት እነዚህን እንቅፋቶችን በመሸሽ በእንግሊዝ ውስጥ የተሰማሩበትን ትልልቅ የኢንቨስትመንት ስራዎችን በመተው ላይ መሆናቸውን ሪፖርት እያደረጉ መሆኑንም ስራ አስኪያጁ አክለዋል፡፡
ጀርመን በከፍተኛ ደረጃ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶችን ከምትልክባቸው ሃገራት መሃል እንግሊዝ ሶስተኛ ደረጃን ትይዛለች፡፡ እንግሊዝ በከፍተኛ ደረጃ ምርቶችን ከምትልክላቸው ሃገራት ጀርመን ሁለተኛ ደረጃን ትይዛለች፡፡
በእንግሊዝ ያሉ የጀርመን ድርጅቶች ከ400 ሺ በላይ ሠራተኞችን ቀጥረው ያሰራሉ፡፡ በጅርመን ያሉ የእንግሊዝ ድርጅቶች ደግሞ ከ220 ሺ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡