ኬንያ የፕላስቲክ ከረጢት ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚያደርገውን ህግ ተግባራዊ ልታደርግ ነው

ኬንያ የፕላስቲክ ከረጢት ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚከለክለውን  ህግ ከዓመታት ቆይታ በኋላ ተግባራዊ  አድርጋለች፡፡

የፕላስቲክ ከረጤት አምራቾች እንደሚሉት ከሆነ የህጉን  መተግበር ተከትሎ  ሰማንያ ሺህ ኬንያውያን ከስራ ገበታቸው ይሰናበታሉ፡፡

ባለፉት አስር ዓመታት ኬንያ በሀገሪቱ የፕላስቲክ ከረጤቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የሚያግደውን ህግ ተግባራዊ ለማድረግ ሰትሞክር ከርማለች፡፡ አሁን ህጉን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሞከረ ያለው እርምጃም ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ህጉ ፀድቆ ይውጣ እንጅ እንዳሁኑ በትኩረት ወደ ተግባር የተገባበት ወቅት እንዳልነበረ ነው ዘገባዎች የሚያነሱት፡፡

አሁን ላይ በኬንያ ተግባራዊ እንዲደረግ የተወሰነው ህግ የፕላስቲክ ከረጢቶችን ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የሚያግደ ሲሆን የፕላስቲክ ከረጤቶችን ሲሸጥ፣ ሲያመርት ወይም በእነሱ እቃዎችን ከቦታ ቦታ ይዞ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ሰው ሰላሳ ስምንት ሺህ የአሜሪካን ዶላር ይቀጣል፡፡  ይህን መክፈል የማይችል ሰው ደግሞ የአራት ዓመት እስራት የሚጠብቀው ይሆናል፡፡

የሀገሪቱ መንግስት እንደሚለው አሁን በፕላስቲክ ከረጢቶች ዙሪያ ተግባራዊ የሆነው ህግ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል አይነተኛ መፍትሄ ነው፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ የአካባቢን ብክለት ያስከትላሉ ተብለው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ በህግ የተከለከሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን የሚያመርቱ አምራቾች ግን በህጉ ላይ ተቃውሞ እያሰሙ ነው፡፡

ይህ ህግ አሁን በኬንያ ተግባራዊ በመደረጉ የዕለት ጉርሳቸውን ከዚህ የስራ ዘርፍ ላይ የሚገኙ ሰማንያ ሺህ ኬንያዊያን ከስራ ገበታቸው እንዲሰናበቱ ምክኒያት ይሆናል  ይላሉ አምራቾች፡፡

ባሳለፍነው አርብ የኬንያ ፍርድ ቤት ይህንን ማስተባበያ አልቀበልም ሲል የፕላስቲክ ከረጢቶች በኬንያ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ከልክያለሁ ብሏል፡፡

በኬንያ ሃያ አራት ሚሊዮን የፕላስቲክ ከረጤቶች በየወሩ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡

ይህ ደግሞ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋሏ ስለሚጣል የኬንያን ስነ ምህዳር ይበክላል፡፡

ቀደም ብለው የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የፕላስቲክ ከረጤቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አግደዋል፡፡  ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ አፍሪካና ሩዋንዳን ለዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

በርካታ ኬንያዊያን ይህን ህግ የደገፉ ሲሆን ጥቂት የማይባሉት ደግሞ ተለዋጭ የፕላስቲክ ዕቃ መያዥያዎችን እና ለስነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የፕላስቲክ አማራጮች እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡

የሀገሪቱን የአካባቢና የመሬት አስተዳደር ባለስልጣን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው ወደ ኬንያ የሚገቡ ተጓዦች ደግሞ ከቀረጥ ነፃ ይዘዋቸው የሚገቡ ማንኛውም አይነት የፕላስቲክ የዕቃ መያዥያዎች በአዲሱ የሀገሪቱ ህግ መሰረት በአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች ጥለው ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ ያስገድዳል፡፡