የሃውቲ አማጽያን በሳዑዲ ዓረቢያ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት ሰነዘሩ

የሃውቲ አማጽያን በሳዑዲ ዓረቢያ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው ተሰማ።

በደቡባዊ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኘው አብሃ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የመንገደኞች ማረፊያ ክፍልን መምታቱ ነው የተነገረው።

በዚህ ሳቢያም 26 ሰዎች መቁሰላቸውን የሳዑዲ ወታደራዊ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

የሃውቲ አማጽያንም በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ ሚሳኤል ማስወንጨፋቸውን አስታውቀዋል።

በየመን የአብድራቡህ መንሱር ሃዲን መንግስት የሚደግፈው ሳዑዲ መራሹ ጥምር ጦር አዛዥ ኮሎኔል ተርኪ አል ማሊኪ ጥቃቱ አለም አቀፉን ህግ የጣሰ ነው በማለት ኮንነዋል።

ጥምር ጦሩም መሰል እንቅስቃሴዎችን ለመግታት እርምጃ ሊወስድ እንደሚችልም ተናግረዋል።

የመን የሃውቲ አማጽያን የአብድራቡህን መንግስት ከስልጣን ለማውረድ እንቅስቃሴ ከጀመሩበት ከፈረንጆቹ መጋቢት 2015 ጀምሮ የጦር አውድማ ሆናለች።

ከዚያን ጊዜ ወዲህም በሳዑዲ የሚመሩ ሃገራት ጥምር ጦር በመመስረት ለማዕከላዊ መንግስቱ ድጋፍ ያደርጋሉ።

በአንጻሩ ኢራን የሃውቲ አማጽያንን በመደገፍ የአብድራቡህን መንግስት ለመጣል የሚደረገውን ጥረት ታግዛለች።

ሃገራት በውክልና በጀመሩት ጦርነት ሳቢያ እስካሁን ከ7 ሺህ በላይ የመናውያን ሲሞቱ በርካቶች ደግሞ ለስደት ተዳርገዋል።

ከዚህ ባለፈም በርካታ ህጻናት በምግብ እጥረትና በርሃብ ህይዎታቸውን አጥተዋል።

የሃውቲ አማጽያን እና ማዕከላዊ መንግስቱ ባለፈው ታህሳስ ወር የተኩስ አቁም ለማድረግና ጦራቸውን ከሶስት የወደብ ከተሞች ለማውጣት ቢስማሙም ግጭቱ ግን ዛሬም እልባት አላገኘም መረጃዉ ቢቢሲ ነዉ።