የአላባማ ግዛት ህጻናትን የደፈሩ እንዲኮላሹ የሚያዝ ሕግ አሳለፈች

በአሜሪካ የምትገኘው አላባማ ግዛት ህጻናትን የደፈሩ በኬሚካል እንዲኮላሹ የሚያዝ ሕግ አሳለፈች።

በሕጉ መሠረት፤ እድሜያቸው ከ13 ዓመት በታች በሆኑ ህጻናት ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ፈጽመው በእስር ላይ የሚገኙ ወንጀለኞች ፍርዳቸውን ሳይጨርሱ ከእስር የሚለቀቁ ከሆነ፤ ከአንድ ወር በፊት የወሲብ ፍላጎታቸውን የሚቀንስ መድሃኒት እንዲወስዱ ይደረጋል።

መድሃኒቱ በእንክብል ወይም በመርፌ መልክ የሚሰጥ ሲሆን በሰውነት ውስጥ የሚገኘውን የቴስቴስትሮን መጠንን ዝቅ በማድረግ የወሲብ ፍላጎንትን በከፍተኛ መጠን ይቀንሳል።

ይሁን እንጂ መድሃኒቱ መወሰድ ሲቆም የወሲብ ፍላጎት ወደነበረበት ይመለሳል።

ከአላባማ ግዛት በተጨማሪ ሉዚያና፣ ፍሎሪዳ እና ሌሎች 4 የአሜሪካ ግዛቶች ይህን መሰሉን ሕግ ተቀብለው ተግባራዊ ያደርጋሉ።

የአላባማ ግዛት አስተዳዳሪ ኬይ ኢቪይ ነች ሰኞ ዕለት በፊርማዋ ሕጉን ያጸደቀችው። ''ይህ በአላባማ የሚገኙ ህጻናትን ለመታደግ አንድ እርምጃ ነው'' ብላለች አስተዳዳሪዋ።

በወንጀል ድርጊቱ ጥፋተኛ የተባሉት ግለሰቦች ለመድሃኒቱ ወጪውን ይሸፍናሉ።

ይህን የሕግ ማዕቀፍ ሥራ ላይ እንዲውል ጫና ያሳደሩት የሪፓብሊካኑ ተወካይ ስቲው ሃረስት ሲሆኑ፤ ጾታዊ ትንኮሳ የደረሰባቸው የሕጻናት ማቆያ ማዕከል ውስጥ ከሚገኙ ልጆች የሰሟቸው ታሪኮች እጅጉን እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።

ይህ ሕግ ተቃውሞ አላጣውም። የአላባማ አሜሪካ ሲቪል ሊብሪቲስ ማህበር ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ራንዳል ማርሻል ለAL.com ሲናገሩ፤ ''ይህን መድሃኒት ሊያስከትለው የሚችለው ጉዳት ምን እንደሆነ አይታወቅም። ግዛቱ በምርምር ደህንነቱ የልተረጋገጠን መድሃኒት በሰዎች ላይ መጠቀም ሲጀምር፤ ከሕገ-መንግሥቱ ጋር የሚጻረር ይመስለኛል።'' ብለዋል።

እ.አ.አ. 2009 ላይ እንግሊዝ ውስጥ በኬሚካል የማኮላሸት የምረምር ፕሮጄክት ላይ ፍቃደኛ የነበሩ እሰረኞች ተሳታፊ ነበሩ።

''ከፍተኛ የሆነ የወሲብ ፍላጎት ወይም ወሲባዊ ምኞት'' አለባቸው የተባሉት እስረኞች፤ መድሃኒቱን ከወሰዱ በኋላ ''በህይወታቸው ላይ አዎንታዊ ለውጥ ተመዝግቧል'' ሲሉ የአዕምሮ ጤና ባለሙያ ዶን ግሩኒን ተናግረዋል።

ደቡብ ኮሪያ እና ኢንዶኔዥያ ይህን መሰል ሕግ ተግባራዊ ያደርጋሉ ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።