የአልቃይዳ መስራች ኦሳማ ቢን ላደን ወንድ ልጅ ሀምዛ ቢን ላደን፣ መሞቱን የአሜሪካ የስለላ ባለስልጣናት መናገራቸው ተገልጿል፡፡
የሀምዛን ቢን ላደን አማሟት እንዴት እና የት እንደሆነ ግን የተባለ ነገር የለም፡፡
የአሜሪካ መንግስት የካቲት ወር ላይ ሀምዛ የት እንዳለ ለጠቆመ የ1 ሚሊየን ዶላር ገንዘብ በጉርሻ መልክ እንደሚሰጥ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
30 ዓመት ይሆነዋል ተብሎ የሚገመተው ሀምዛ ቢን ላደን በአሜሪካና ሌሎች ሀገራት ላይ ጥቃት እንዲፈፀም የሚጠይቅ የተንቀሳቃሽ ምስልና ድምፅ መልዕክት አስተላልፎ እንደነበር ተገልጿል፡፡
በጉዳዩ ላይ ረቡዕ ዕለት በሪፖርተሮች የተጠየቁት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም እና የኋይት ሃውስ የሀገር ደህንነት አማካሪ ጆን ቦልተን አስተያየታቸውን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ሀምዛ ቢን ላደን እ.ኤ.አ.በ 2011 ግንቦት ወር ላይ በፓኪስታን በአሜሪካ ልዩ ሀይል የተገደለውን የአባቱን ገዳዮች ለመበቀል ጂሃዲስቶች ጥቃት እንዲፈፅሙ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን÷ ሳዑዲ አረቢያ ዜግነት እንደነጠቀችውም አይዘነጋም፡፡
የአሜሪካ መንግስት እንደሚለው እ.ኤ.አ.በ 2011 በፓኪስታን አቦታባድ በአባቱ ቤት በተደረገው ፍተሻ የተገኙ ሰነዶች እንደሚያሳዩት ሀምዛ አልቃይዳን እንዲመራ ታጭቶ ነበር።
(ምንጭ፦ ቢቢሲ)