በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመቋቋም ለመሰብሰብ ከታቀደው የሰብል ምርት 95 በመቶ ማሳካት መቻሉን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በዞኑ 9ሺህ 150 አርሶአደሮችን በክላስተር በማደራጀትና ግብዓቶችን በማከፋፈል ምርትና ምርታማነትን ማስቀጠል መቻሉ ነው የተገለጸው፡፡
የምዕራብ ሸዋ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከበደ ደበሎ በዞን ደረጃ በጤፍ፣ ስንዴና በቆሎ ምርቶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደተሰራ ገልጸው፣ ከታቀደው የሰብል ምርት 327 ሺህ ሄክታር መሬት በሰብል መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ የማዳበሪያና የኬሚካል እጥረት በዞኑ ይገጥም እንደነበር የተናገሩት ኃላፊው፣ አርሶአደሮችን በስልጠና በታገዘ መልኩ በክላስተር ማደራጀት በመቻሉ የግብዓት እጥረቶችን ማቃለል እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡
በ2012 ዓ.ም መጋቢት ወር ወደ ኢትዮጵያ የገባው ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በግብርናው ዘርፍ ለአርሶአደሩ ስልጠና እና ክትትል ከማድረግ አንፃር የፈጠረው ተጽዕኖ ቢኖርም ቤት ለቤት ስልጠና በመስጠት እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ጫናውን መቀነስ መቻሉ ተገልጿል፡፡
በዘንድሮ ዓመት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ መከሰቱን ተከትሎ በሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ቀደም ብሎ አጨዳ መጀመሩንም የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ከበደ ገልጸዋል፡፡
በምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጀርሳ ለፌ ወረዳ የጨለለቃ ቀበሌ ገበሬ ማህበር አርሷአደር አባ ሊቃ በበኩላቸው፣ በክላስተር ተጀራጅተው ሰብል በማምረታቸው ትርፋማ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
(በሀኒ አበበ)