በጎሎልቻ ወረዳ ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የኮንትሮባንድ እቃ በቁጥጥር ሥር ዋለ

በምስራቅ ባሌ ዞን ጎሎልቻ ወረዳ ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ሽመልስ ገበየሁ እንደገለጹት፤ በቁጥጥር ሥር የዋሉት አዳዲስ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ አልባሳት፣ ሽቶና ሌሎችም እቃዎች ናቸው።

ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. እኩለ ቀን አካባቢ የተገኙት እነዚህ የኮንትሮባንድ እቃዎች የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3- 03214 አዲስ አበባ እና ኮድ 3 – 36058 አዲስ አበባ በሆኑ አይሱዙ ተሽከርካሪዎች ተጭነው መሆኑን ተናግረዋል።

ተሽከርካሪዎቹ ከሶማሌ ክልል ከገይዳ ወደ ሃረርጌ ለመጓዝ ሲሰናዱ በጎሎልቻ ወረዳ ድሬ ሼህ ሁሴን ቀበሌ በቁጥጥር ስራ ማዋል መቻሉን አስረድተዋል።

አሽከርካሪዎቹ ለጊዜው ቢሰወሩም ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ክትትል እያደረገባቸው እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የአገር ኢኮኖሚንና የፀጥታ ሥራን እየተፈታተነ የሚገኘውን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመግታት ሁሉም የተቀናጀ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የወረዳው ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋለውን የኮንትሮባንድ እቃ ዛሬ በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ለሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስረክቧል።

እቃዎቹን የተረከቡት የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የህግ ተገዢነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዴሳ ለማ በበኩላቸው ህገ ወጥ ንግድ መንግስት ማግኘት የሚገባውን ገቢ የሚያሳጣ እና ህጋዊ ነጋዴዎችን ከውድድር በማስወጣት በንግድ ሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድር አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ሁሉም ህገ ወጥ ድርጊቱን ለመከላከል እንዲሰራ ጠይቀዋል።

(ምንጭ፡ኢዜአ)