ተጋሩ የኢትዮጵያዊያን ድርጅት በትግራይ ወቅታዊና መጻኢ ጉዳዮች ዙሪያ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖሊቲካ ፓርቲ አመራሮችና የሲቪክ ማህበራት ጋር ውይይት አድርገዋል።
የኢትዮጵያዊያን ተጋሩ ድርጅት የቦርድ ሰብሳብ አቶ ዩሐንስ ጎይቶም ውይይቱን ማድረግ የተፈለገው በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ግልፅ እና አሳታፊ ለማድረግ ነው ብለዋል።
ለውጡን ተከትሎ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች እንዲፈቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ማህበረሰቡ ጋር በመተባበር ችግሮቹ እንዲፈቱ እና አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከሃማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከፖሊቲካ ፓርቲዎች እና ዜጎችን ያካተተ የመማክርት ጉባኤ መቋቋም ስላለበት ለባለድሻ አካላት ለማስገንዘብ መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የትግራይ ህዝብ በተጀመረው የለውጥ ጉዞ ፖሊቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፍትህ እንዲቀዳጅ ተባብረን መስራት አለብን ብለዋል አቶ ዮሐንስ።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ነብዩ ሰሁል ሚካኤል እንዳሉት በትግራይ በሚደረገው መልሶ የማቋቋም ተግባር በክልሉ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ፓርቲ እና የሲቪክ ማህበራት የበኩላቸውን ለመወጣት እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው ።
በትግራይ ክልል በሚደረግ ለውጥ ሁላችንም አብረን መጓዝ አለብን ያሉት አቶ ነብዩ ለውጡ ሁሉን አቃፊ መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል ያለውን ችግር መፍታት የሚቻለው በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የዴሞክራሲ ምሰሶ በሆኑት የሲቪከ ማህበራት መሆኑንም አብራርተዋለ።
የሲቪክ ማህበራትም በቀጣይ በክልል በሚደረጉ የለውጥ ጎዞዎች የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልፀው፤ ፓርቲውም ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው የህወሐት ጁንታ በትግራይ ክልል ለሶስት አስርት አመታት ያደረሰውን ችግር መፍታት የሚያቻለው ተቀራርቦ በመነጋገር ነው ብለዋል።
የትግራይን ህዝብ ችግር መፍታት የሚቻለው የፖሊቲካ ፓርቲ በማቋቋም ብቻ ሳይሆን የሲቪክ ማህበራትንም በማደራጀት መሆኑን ገልጸዋል።
የሕወሐት የጥፋት ቡድን የትግራይን ህዝብ ለተለያዩ ችግሮች መዳረጉን አስታውሰው ችግሩን ለመፍታት ሁሉም መረባረብ አለበት ማለታቸውን ኢዜአ ዘገቧል።