የጁንታው ቡድን የህግ ማስከበር ዘመቻው በንጹሃን ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ አድርጎ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት ላይ ይገኛል- አምባሳደር ግርማ ተመስገን

“የጁንታ ቡድን የህግ ማስከበር ዘመቻው በንጹሃን ላይ ያነጣጠረ የዘር ማጽዳት  እንደሆነ አድርጎ በሚከፍላቸው የመገናኛ ብዙሃን እና ግለሰቦች በኩል የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት ላይ ይገኛል” ሲሉ በቱርክ የኢትዮጰያ አምባሳደር ግርማ ተመስገን  ገለጹ።

አምባሳደር  ግርማ  ተመስገን በወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳዮች እና ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ስላላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዙሪያ ከአናዶሉ ኤጀንሲ ጋር  ቆይታ አድርገዋል።

የጁንታ ቡድን በትግራይ ክልል ሆኖ ለ20 አመታት  የሀገር ሉዓላዊነት ሲያስከብር በነበረው መከላከያ ሰራዊት ላይ  ይቅር የማይባል ጥቃት ከመፈጸሙ በተጨማሪ በተለያዩ ቦታዎች ንጹሃኖች እንዲገደሉ አድርጓል ብለዋል፡፡

አምባሳደር ግርማ መንግስት ወደ ህግ ማስከበር እርምጃው ተገዶ እንዴት እንደገባ ሲገልጹ ፤የጁንታው ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ አረመኔያዊ ጥቃት ፈጽሞ ”ቀይ መስመር ማለፉን” ተናግረዋል።

የህወሃት ቡድን የጭካኔ  ድርጊት ይህ ሆኖ ሳለ መንግስት የወሰደው ወታደራዊ ዘመቻን  በተሳሳተ መንገድ የሚወስዱ አካላት ትክክለኛውን የዘመቻው መነሻ መረዳት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

የህግ ማስከበር ዘመቻው መቀሌ ከተማን በመቆጣጠር እንደተጠናቀቀ ያስረዱት አምባሳደር ግርማ ተመስገን በአሁኑ ወቅት አጣዳፊዎቹ የመንግስት ተግባራት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም፣ሰብዓዊ ዕርዳታ ማቅረብ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለዚህም የመሰረተ ልማቶችን እንደገና በመገንባት ከተቋቋመው ጊዜያዊ  አስተዳደር ጋር ስራዎች እየተሰሩ ነው።

አምባሳደሩ የህወሃት ቡድን የመንግስትን የህግ ማስከበር እርምጃ  አለማቀፋዊ ገጽታ ለማላበስ ሞክሯል ብለዋል።

ቡድኑ ግጭቱን አለም አቀፋዊ ለማስመሰል ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱን እና ኢጋድና የአፍሪካ ህብረት ጉዳዩ የሃገር ውስጥ

የህግ ማስከበር ዘመቻ መሆኑን እንደተገነዘቡ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በቱርክ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የሚደነቅ መሆኑን ለአናዶሉ ኤጀንሲ ገልጸዋል።

አክለውም ቱርክ በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ቀድመው ከተረዱ ሃገራት መካከል አንዷ መሆኗን ተናግረዋል።

ለዚህም ያስረዱት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ ከኢትዮጵያ አቻቸው አቶ  ደመቀ መኮንን ጋር በዚሁ ጉዳይ የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

አምባሳደሩ የሁለቱ ሀገራት ትብብር  የረጅም ጊዜ አጋርነትና የጠንካራ ግንኙነት ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ቱርክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 125ኛ አመት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አምባሳደር ግርማ ተመስገን ማናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡