ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ በሰላም ማስከበርና ጠንካራ ዲፕሎማሲ ምሳሌ እና ተጠቃሽ መሆን የምትችል ሀገር ናት – ምሁራን  

እንዳለ ንጉሴ

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ በሰላም ማስከበር እና በጠንካራ ዲፕሎማሲ ምሳሌ እና ተጠቃሽ መሆን የምትችል ሀገር መሆኗን ዋልታ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ እና ሱዳን ወንድማማች ህዝቦች እንደመሆናቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ምንም አይነት ግጭት ሊከሰት እንደማይችል የሚገለጹት ምሁራን፣ ከጀርባ ሆኖ ይህንን የሚጠነስስ ኃይል አይሳካለትም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ዲፕሎማሲና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር እንዳለ ንጉሴ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ምርምርና ጥናት ተቋም መምህር መሀመድ ሀሰን በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ ያለው ውጥረት አሁንም እየተስተዋለ ቢሆንም፣ ውጥረቱ እንዲከሰት ያደረገው የውጭ ሀይል የሱዳን የውስጥ አለመረጋጋትን በመጠቀም ግጭቱን እያባባሰ እንዳለ ገልጸዋል፡፡

በውጭ ኃይሎች እንዲህ አይነት ትንኮሳ ኢትዮጵያ ላይ የሚቀነባበረው ኢትዮጵያውያን ለጋራ ሰላማቸው ምን ያህል ተባባሪ ህዝቦች መሆናቸውን ካለማወቅ የተነሳ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

መምህር መሀመድ ሀሰን

ግብጽ በአሁን ሰአት በርካታ የውስጥ ችግር ያሉባት ሀገር እንደመሆኗ ሱዳንን ልታጋፍጣት እንጂ ልትረዳት እንደማትችል ራሱ የሱዳን መንግስት ጠንቅቆ ያውቃል ያሉት ምሁራን፣  ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ግጭት ውስጥ የመግባት ፍላጎት ፈጽሞ እንደለላትም ጠቁመዋል፡፡

ይህን የድንበር ላይ ግጭት ራሳቸው ሱዳን እና ኢትዮጵያ በውይይት ሊፈቱት የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሰለም እና መረጋጋት እንዲመጣ ያላሰለሰ ጥረት ስታደርግ የቆየች ሀገር ስትሆን፣ በተለይም ይሄ ጥረቷ በሱዳን ፍሬ አፍርቶ ሱዳናውያን በይፋ በአደባባይ በመውጣት ኢትዮጵያን ያመሰገኑበት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

በሁለቱ ሀገራት መንግስታት መካከል ያለው ዲፕለማሲያዊ ግንኙነት አሁን በጠንካራ ትስስር እንደቀጠለም ተመልክቷል፡፡ ይሁን እንጂ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያልተካለለ ድንበር በመኖሩ ላለፉት ረዥም አመታት ግጭት ሊባል የማይችል ጉዳይ ሲንጸባረቅ መቆየቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማሳወቁም የሚታወስ ነው፡፡

(በሜሮን መስፍን)