ቦርዱ ቀጣዩን ምርጫ ተአማኒ የሚያደርጉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያጠናቀቀ ነው

 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መጪውን ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ የሚያደርጉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያጠናቀቀ እንደሚገኝ ገለጸ።

የቦርዱ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ስራ አስኪያጅ ወ/ት ሶሊያና ሽመልስ እንደገለጹት፤ ቦርዱ ቀጣዩ ምርጫ ቀደም ሲል ከተካሄዱ ምርጫዎች ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ ሆኖ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያደርጉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያጠናቀቀ ይገኛል።

ምርጫው ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የምርጫ ቁሳቁሶች 90 በመቶ ተገዝተው መጠናቀቃቸውን ያመለከቱት ስራ አስኪያጇ፣ የተገዙት የምርጫ ቁሳቁሶቹና ህትመቶች ከዚህ በፊት ምርጫ ከተደረገባቸው ቁሳቁሶችና ህትመቶች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እንደሆኑ አስታውቀዋል።

የድምጽ መስጫ ወረቀቶቹና የመራጭ ካርዶቹ ደግመው መታተም የማይችሉ፣ ከተነካኩ የሚያስታውቁ፣ የራሳቸው የሆነ ቀሪ ያላቸው፣ ኮፒ ለመደረግ የሚያስቸግሩ እንዲሁም የድምጽ መስጫ ሳጥኖቹ አስተማማኝና መራጩ ድምጽ ሲሰጥ በነጻነት ለመስጠት የሚያስችል መከለያዎች ያሉት እንደሆነም ጠቁመዋል።

(ምንጭ፡- ኢፕድ)