የህዝቡን የቆየ አብሮነት ለማስቀጠል አሳታፊና ተከታታይነት ያለው ሥራ መስራት እንደሚገባ ምክር ቤቱ አሳሰበ

የኢፌዴሪ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ስብሰባ አካሂዷል፡፡

ምክር ቤቱ በውሎው ታህሳስ 15 ቀን 2013 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በመተከል ዞን እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የተፈጸመውን የግፍ ግድያ አስመልክቶ የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

በዚህም ቋሚ ኮሚቴዎቹ ለምክር ቤት አባላት ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ በዚህም መንግስት ክትትል እና እርምጃ መውሰድ እንደሚገባምው ተናግረዋል፡፡

የህበረተሰቡን የቆየ አብሮነት ለማስቀጠል ህዝቡን ያሳተፈ ተከታታይነት እና ቀጣይነት ያለው ስራ መሰራት ይኖርበታልም ሲል ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡

በውይይቱ መንግስት ተከታታይነት ያለው የግንዘቤ ማስጨበጫ ስራዎች በአካባቢዎቹ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ዜጎች በህገ-መንግስቱ የተቀመጠላቸውን መብቶች መጠቀም እንዲችሉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረኮች መፈጠር አለባቸው ተብሏል፡፡

በመተከል እና አካባቢው ለተፈጠረው የግፍ ግድያን አስመልክቶ መንግስት በየደረጃው ያሉ አመራሮችን እና በወንጀሉ የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴዎች ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያን ሰላም እና እድገት የማይፈልጉ የውጭ የጥፋት ኃይሎች ከአንድ አንድ የሚዲያ አካላት ጋር በመቀናጀት የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ በማደናቀፍ እና የተደበቀ አላማቸውን ለማሳካት ሲጥሩ መቆየታቸውን ኮሚቴዎቹ መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡

(በሜሮን መስፍን)