የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ነው – ኮሚሽኑ

ችግር በተከሰተባቸው የሀገሪቱ ክፍል የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለፀ።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከሚሽነር ምትኩ ካሳ ኮሚቴው የተለያዩ የመንግስት ተቋማትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ያቀፈ መሆኑን ገልፀው ምግብ ነክ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ እና የመልሶ ማቋቋም ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

2.5 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎችን መመገብ የሚችል 311 ሺህ 526 ኩንታል እህል እርዳታ የተዘጋጀ ሲሆን 1.8 ሚሊየን ለሚደርሱ ዜጎች የአስቸኳይ እርዳታ ልማትና መልሶ ማቋቋም ስራ ተደራሽ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን በሰባት ወረዳዎች 97ሺህ 613 ዜጎች መፈናቀላቸውንም ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሸ ሰጪ ማስተባበሪያ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት አቶ ምትኩ 51ሺህ 408 ኩንታል የዱቄትና የበቆሎ እንዲሁም አልባሳትና ማብሰያ ቁሳቁሶች እየቀረቡ መሆናውን አብራርተዋል፡፡

(በብርሀኑ አበራ)