በታንዛንያ እስር ቤቶች የነበሩ 80 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ሊመለሱ ነው

በታንዛንያ እስር ቤቶች የነበሩ 80 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ በታንዛንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዮናስ ዮሴፍ ገለጹ።

እ.አ.አ በ2021 በእስር ቤቶቹ የሚገኙ 1 ሺህ 800 ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ መታሰቡንም አምባሳደሩ ጠቁመዋል።

በታንዛንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዮናስ ዮሴፍ፤ በዳሬሰላም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሕዳር ወር 2013 ዓ.ም በሞሮጎሮ፣ ታንጋ፣ ፕዋኒና ባጋሞዮ ግዛቶች ባደረገው ምልከታ ከ1 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን በእስር ቤቶች እንዳሉ መግለፃቸው ይታወሳል።

ኤምባሲው በአራቱ ግዛቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ይቅርታ ተደርጎላቸው እንዲፈቱና ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ከታንዛንያ የኢሚግሬሽንና ማረሚያ ቤት ተቋም ጋር ሲነጋገር መቆየቱንና ተቋሙም በጎ ምላሽ መስጠቱን አምባሳደሩ ተናግረዋል።

ተቋሙ ኤምባሲው ዜጎቹን ወደ አገር ቤት ለመመለስ የሚያስፈልገውን ገንዘብ አሰባስቦ ዝግጁ ሲሆን ኢትዮጵያዊያኑን ለመፍታት ፈቃደኛ እንደሆነም አመልክተዋል።

“ኤምባሲው ዜጎቹ ከእስር ተፈትተው ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት የሀብት ማሰባሰብ ሥራ ነው” ብለዋል።

በታንዛንያ የሚገኘው የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) ቢሮ ከእስር የተለቀቁ 80 ኢትዮጵያዊያን በሁለት ሳምንት ጊዜ ወስጥ ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን ገንዘብ እንደሚሸፍንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያውያኑ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የኢትዮጵያ መንግስት፣ ዳሬሰላም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅትና ሌሎች የልማት አጋሮች ጋር በጋራ እየሰሩ ነው።

“ኤምባሲው በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች የሰብአዊ መብታቸው መጠበቁንና አስፈላጊውን አገልግሎት እያገኙ ስለመሆኑ የቅርብ ክትትል እያደረገ ይገኛል” ብለዋል።

በታንዛንያ እስር ቤት የሚገኙ 1 ሺህ 800 ኢትዮጵያዊያንን በፈረንጆቹ 2021 ሙሉ ለሙሉ ለመመለስ ኤምባሲው ማቀዱን ጠቁመዋል።

አሁንም ወደ ታንዛንያ የሚገቡ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ የገለጹት አምባሳደር ዮናስ፤ ዜጎች በጉዟቸው ወቅት በደላሎች እንግልትና ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን አመልክተዋል።

የሚሰሰዱት ዜጎች ወጣቶች መሆናቸውን የገለጹት አምባሳደር ዮናስ “በትንሹ ለደላሎች እስከ 150 ሺህ ብር ይከፍላሉ” ብለዋል።

ወጣቶቹ በሚከፍሉት ገንዘብ በሚኖሩበት አካባቢ ኑሯቸውን ማሻሻል ስለሚችሉ መንግስት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት ተቋማትና የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው የአመለካከት ለውጥ ላይ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት በዳሬሰላም የተከፈተው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከ3 ሺህ በላይ ዜጎችን ከእስር አስፈትቶ ወደ አገር ቤት መመለሱን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።