የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ዛሬ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እንደሚለቁ ተገለጸ።
ኮንቴ ሥልጣናቸውን የሚለቁት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በተከሰተው ምስቅልቅል ያሳዩት አስተዳደር ደካማ ነው በሚል ከተተቹ በኋላ ነው ተብሏል።
በጣሊያን 85 ሺህ ሰዎች በተህዋሲው መሞታቸው ይታወሳል።
ኮንቴ ሥልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ የአገሪቱ ፕሬዝዳንቱ ሌላ አዲስ ጠንካራ መንግሥት እንዲመሠርቱ ዕድሉ ይሰጠኛል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።
በፕሬዝዳንቱ ይህ ዕድል ሲሰጣቸው ምክር ቤት ከገቡ ፓርቲዎች ጋር ተነጋግረው አዲስ ጠንካራ ጥምረት ያለው መንግሥት መሥርተው ወደ ሥልጣን ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጁሴፔ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ግን መንግሥት የመመሥረቱን ኃላፊነት ፕሬዝዳንቱ ለሌላ ሰው አሳልፈው ይሰጣሉ።
ኮንቴ ከ2018 ጀምሮ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቆይተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነቀፌታ በርትቶባቸው በታችኛው ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት የመተማመኛ ድምጽ ተሰጥቶባቸው በሥልጣን የሚያስቀጥለውን መተማመኛ ድምጽ ማግኘት ችለዋል።
ይህ የመተማመኛ ድምጽ እንዲሰጥባቸው የሆነው የቀድሞው የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ማቲዮ ሬንዚ የሚመሩትና ትንሹ ‘ኢታሊያን ቪቫ’ ፓርቲ ከኮንቴ መንግሥት ጥምረት ራሱን በማውጣቱ ነው።
ገለልተኛኛ ከፖለቲከኛ ይልቅ ሙያተኛ ናቸው የሚባሉት ኮንቴ ተከታታይ ሁለት የመንግሥት አስተዳደሮችን መርተዋል።
ለ15 ወራት ያህል ኤም5ኤስ የተባለው ፓርቲና ቀኝ አክራሪው የማቲዯ ሳልቪኒ ፓርቲ የመሰረቱትን ጥምረት መርቷል።
ከዚያ በኋላ ደግሞ ኤም5ኤስ እና ዲሞክራቲክ ፓርቲዎች የመሰረቱትም የጥምር መንግሥት ለመምራት ችለዋል።
በጣሊያን በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ አዲስ አገር አቀፍ ምርጫ ማድረጉ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ጆሴፔ ኮንቴ አዲስ ጠንካራ የጥምር መንግሥት መሥርተው ወደ ሥልጣናቸው ይመለሳሉ የሚል ትልቅ ተስፋ እንዳለ ቢቢሲ አስነብቧል።