የአውሮፓ ህብረት የኮቪድ-19 ክትባት ወጪ ንግድ መመሪያን ሊያጠብቅ ነው

የአውሮፓ ህብረት የኮቪድ-19 ክትባት ወጪ ንግድ ላይ ያሉ መመሪያዎችን እንደሚያጠብቅ አስጠንቅቋል።

በህብረቱ የጤና ኮሚሽነሯ ስቴላ ካይራኪድስ እንዳሉት የአውሮፓ ህብረት “ዜጎቹን ለመጠበቅ ማንኛውንም አስፈላጊ እርምጃዎች ይወስዳል” ብለዋል።

የአባላት አገሮቹን ወክሎ ክትባቶቹን እየገዛ ያለው የአውሮፓ ህብረት ክትባቶቹን እያከፋፈለ ያለበት መንገድ ጋር በተያያዘ ትችት እየቀረበበት ይገኛል።

ባለፈው ሳምንት በዩኬ የመድኃኒት አምራች የሆነው አስትራዜኔካ ባጋጠመው የምርት ችግር ምክንያት በወቅቱና በሚፈለገው መጠን ክትባቶችን ማቅረብ እንደማይችል ለአውሮፓ ህብረት አስታውቆ ነበር።

ለአውሮፓ አገር አባላት ቃል የተገባው የክትባት አቅርቦት መጠን በቂ ባለመሆኑ ውዝግብ ተነስቷል።

አስትራዜኔካ ለ27 የህብረቱ አባል አገራት ሊያቀርበው ከነበረው መጠን በከፍተኛ መጠን ቀንሶ ነው ያቀረበው ተብሏል።

ኮሚሽነሯ ከአስትራ ዜኔካ ጋር ያደረጉት ውይይት ግልፅ ያልሆነና በቂ ማብራሪያ የሌለው ነው ሲሉ በኩባንያው አሰራር የተሰማቸውን ቅሬታ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

“የአውሮፓ አባል አገራት በአንድነት ቆመናል። ክትባት አምራች ድርጅቶች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት ማህበራዊ እንዲሁ ህጋዊ ግዴታ አለባቸው” ብለዋል።

ይሄ ውዝግብ የዩኬ የክትባት አቅርቦት መጠን ላይ ጫና እንደሚያደርስ ተገልጿል። ይህም በአሜሪካና በጀርመን የበለፀገው የፋይዘር ባዮንቴክ ክትባት ጋር የተያያዘ ነው።

በቤልጂየም ያለው የፋይዘር ቅርንጫፍ ለዩኬ ክትባቱን እያቀረበ እንዳለ እና የዩኬ መንግሥት ከክትባት አቅራቢዎቹ ጋር በቅርበት እየሰራሁ ነው ብሏል።

“የክትባት አቅርቦታችንና የሚጠበቀው የክትባት መጠን በመጀመሪያ ዙር ለምናስበው አራት ቅድሚያ ቡድኖች በቂ ነው” በማለት የመንግሥት ቃለ አቀባይ ተናግረዋል።

በአንዳንድ የአውሮፓ ክፍሎች የፋይዘር-ባዮኤንቴክ ክትባት አቅርቦት በመቀነሱ ምክንያት ክትባቱ በመጓተት ላይ ነው።

ይህንን ተከትሎ አንዳንድ አገራት ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስዱ በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።

ከኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ጋር ክትባቱን የሚሠራው አስትራዜኔካ ይፋዊ የሆነ መግለጫ ከመስጠት ተቆጥቧል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።