ኢትዮጵያ በታሪክ ለቀጠናዊ እድገት እና ኑሮ መሻሻል የነቃ ተሳትፎ እንደነበራት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
የፕላን እና ልማት ኮሚሽን የኢትዮጵያ 10 አመታት የልማት እቅድ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ገለፃ እየተደረገ ነው።
በፕሮግራሙ ላይ በኢትዮጵያ የሚገኙ የውጭ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም የአለም አቀፍ እና ክልላዊ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ኢትዮጵያ በታሪክ ለቀጠናዊ እድገት እና ኑሮ መሻሻል የነቃ ተሳትፎ እንደነበራት አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ከመጣ በኋላ በርካታ የፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች ተከናውኗል ያሉት ፕሬዝዳንቷ፣ አዲስ የኢኮኖሚ ሞዴል በመከተል የግሉ ዘርፍን አሳታፊ ያደረገ አሰራር ተዘርግቷል ብለዋል።
ሀገሪቱ መሪ እቅድ በማዘጋጀት እና በመተግበር ረገድ አዲስ አለመሆኗን ገልጸው፣ በቀጣይ 10 አመታት የሚተገበረው የልማት እቅድ ግልፅ ግቦችን ያነገበ መሆኑን አንስተዋል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ አሁን ላይ ፍትሀዊ የማክሮ ኢኮኖሚ አለመኖር፣ የምርት እጥረት፣ ድህነት፣ የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ እንዲሁም የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እና የአየር ንብረት ለውጥ የኢኮኖሚ ፈተና መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቀጣይ 10 አመታት እቅድ ድህነትን ለመቀነስ፣ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ለመፍጠር፣ ምርታማነትን ለመጨመር፣ የጤና እና መሰል አገልግሎቶችን በበቂ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ለእቅዱ ተግባራዊነት እንዲሁም የተቋማትን ጥራት ለማሻሻል እና የኢኮኖሚ አቅምን ለመገንባት በሚደረገው ሂደት የአለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ፣ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ቀጣይ 10 አመታት እነዚህ ዘርፎች በቴክኖሎጂ አቅም በመገንባት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት መታቀዱ ተገልጿል፡፡
(በደረሰ አማረ)