የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እና የፌደራል መሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ በዋናነት የኮርፖሬሽኑን መሰረተ-ልማት ወደ ዲጂታል ስርአት እንዲገባ የማድረግ እና የሳይበር ልማት ስትራቴጂክ ፍኖተ-ካርታ የማዘጋጀት እንዲሁም የመረጃዎቹን ደህንነት ማስጠበቅን ያካተተ እንደሆነ ተገልጿል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው በስምምነቱ ወቅት እንዳሉት መሬት ዋነኛ ሀብት በመሆኑ መረጃውን በተገቢው መንገድ መጠቀም እና ማስቀመጥ ለሀገር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡
መረጃ አሁን ባለንበት ዘመን ትልቁ እና ቁልፍ መወዳደሪያ እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ሹመቴ፣ ይህንን መረጃ ደህነነቱን ለማስጠበቅ እና ለመጠቀም የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን በሚያከናውናቸው ስራዎች ላይ ኤጀንሲው በጋራ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
የፌደራል መሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሌንሳ መኮንን በበኩላቸዉ ትልቅ ሀብት የሆነው የመሬት ነክ መረጃ መያዝ ሀገሪቱ በምታከውናቸው የመሰረተ- ልማት ስራዎች ላይ ጥራት ያለው ውሳኔ ከመስጠት ባለፈ ደህንነቱን ለማስጠበቅ ያለውም ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ከኤጀንሲው ጋር የተደረገው ስምምነት ኮርፖሬሽኑ በቴክኖሎጂ ራሱን ለማዘመን በሚያከውናቸው ስራዎች ላይ ማእከል ያደረገ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በተለይ መረጃን ደህንነቱን ለማስጠበቅ ያለመ ነው ማለታቸውን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡