ከ22 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ያበሩስ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት ተመረቀ

የመማር ማስተማር ስራን ምቹ በማድረግና የትምህርት ጥራት በማረጋገጥ፣ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎች ለማፍራት የህብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር አሰታወቀ፡፡

በህብረተሰብና በመንግስት ድጋፍ በተገኘ ከ22 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ያበሩስ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተመርቋል፡፡

በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙት ዶ/ር ኢንጂነር ወንድሙ ተክሌ ትምህርት ቤቶች ያለ ብሄርና ሀይማኖት ልዩነት ብሄራዊ አንድነትን የሰነቁ ብቁ የሀገር ተረካቢ ዜጎች የምናፈራባቸው መሆኑን አስታውሰው፤ ብሄርተኝነትና ጥላቻን ማስወገድ ካልተቻለ ዩኒቨርስቲ ገብቶ መማርም ሆነ መመራመር ለሀገሪቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ዋጋ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

በፍቅር የምንኖርባት ሀገር እንዲኖረን የጋራ ጥረት ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር ወንድሙ  በወልቂጤ ከተማ ባለፉት አመታት ተጀምረው በተለያዩ ምክንያቶች የተጓተቱ የልማት ፕሮጀክቶችም ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከመንግስት ጎን በመቆም ልማቱን ማፋጠን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ገብረመስቀል በበኩላቸዉ ያበሩስ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ከ1973 ጀምሮ ብቁና ተወዳደሪ ዜጎችን በማፍራት በሃገር ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡

ከንቲባው አያዘውም ለምረቃት የበቃውን የተማሪዎች መማሪያ ህንፃው የመማር ማስተማር ስራውን ምቹ በማድረግ ሚናው የጎላ በመሆኑ አስፈላጊውን ግብዓት እንዲሟላለት የከተማው ነዋሪዎች፣ በሀገር ውስጥና በውጪ የሚኖሩ የትምርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪዎች እንዲሁም ባለሃብቶች አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ያበሩስ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ገዛኸኝ ከበደ ትምህርት ቤቱ እስከ 4ሺ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኘ ተናግረዋል፡፡
በአንድ ክፍል ከ90 በላይ ተማሪዎችን በማስቀመጥ የመማር ማስተማር ስራው ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ትምህርት ሲሰጥ እንደነበር ተናግረው በተለይም የኮቪድ-19  ስርጭት እየተስፋፋ ባለበት አሳሳቢ ወቅት የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ አስቸጋሪ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል በአንድ ክፍል በርካታ ተማሪዎች ታጭቀው ትምህርታቸዉን በአግባቡ ለመከታተል ሲቸገሩ እንደነበር ተናግረው አዲሱ ህንጻ  በመማር ማስተማር ስራው ላይ የሚታየውን የቦታ ጥበት ችግር በመፍታት ሚናው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል ፡፡

ደረጃውን የጠበቀ የመማሪያ ክፍሎች እና ምቹ አካባቢ መፈጠሩ ለትምህርት ጥራትና ውጤታማነት ያለዉ ሚና የጎላ መሆኑን ተማራዎቹ ተናግረዋል፡፡

የምርቃ ስነስርአቱ በሃገር ሽማግሌዎች ምርቃት የተጀመረ ሲሆን ለህንጻ ግንባታው ከፍተኛ አስተዋጾ  ያደረጉ ባለድርሻ አካላት ሽልማት ተበርክቷል፡፡