የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ለሰራተኞቹ የብድር አገልግሎት አመቻቸ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ በጋራ በመሆን ለሰራተኞቹ የብድር አገልግሎት አመቻቸ፡፡
የአየር መንገዱ ቀዳማዊ የሰራተኞች ማህበር በአየር መንገዱ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ተመጣጣኝ በሆነ ወለድ የሚከፈል የብድር አገልግሎት ከኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ጋር ስምምነተ አድርጓል።
ስምምነቱ ለሰራተኞች የመኪና እና መኖሪያ ቤት የብድር ግዢ የሚያመቻች መሆኑ ተነግሯል።
የኢትዩጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም አየር መንገዱ ያለው ሀብት በስሩ ያሉት ሰራተኞቹ በመሆናቸው፣ የሰራተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በዚህም አየር መንገዱ 1ሺህ 200 የሚደርሱ ቤቶችን በመስራት ለሰራተኞች ያከፋፈለ ሲሆን፣ በቀጣይ በግንባታ ላይ ያሉ 11ሺህ አፓርታማዎች ተጠናቀው ለሰራተኞች ይረከባሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀዳማዊ የሰራተኞች ማህበር ሀላፊ አቶ ተሊላ ደሬሳ በበኩላቸው፣ አዲሱ ስምምነት ለሰራተኛው መልካም እድልን እንደሚፈጥር ገልፀዋል።
የብድር ስምምነቱ በኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በአየር መንገዱ ቀዳማዊ የሰራተኞች ማህበር መካከል ተደርጓል።
(በቁምነገር አህመድ)