የካቲት 12/ 2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የወታደራዊ ደህንነቶች መረጃ ልውውጥን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት የስምምነት ፊርማ ተፈራረሙ።
የስምምነት ፊርማው የተፈረመው በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሞች ነው።
የፊርማ ስነ-ስርዓቱ የተደረገው 11ኛው የሁለቱ ሀገሮች የጋራ የኢታማዦር ሹሞች ስብሰባ በዛሬው ዕለት በመኮንኖች ክበብ በተጠናቀቀበት ወቅት ነው፡፡
በደቡብ ሱዳን ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ጆንሰን ጁማ ኡኮት የተመራው የደቡብ ሱዳን የመከላከያ ከፍተኛ ጀነራል መኮንኖች ልዑክ በትናንትናው ዕለት ከኢፌዴሪ አቻው ጋር ተገናኝቶ በሁለቱ ሀገሮች የጋራ ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ መምከሩ ይታወቃል፡፡
በዛሬው ዕለት ደግሞ በመከሩባቸው ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደርሰው የፊርማ ስነ ስርዓት አከናውነዋል፡፡
በዚህም መሰረት፣ በሁለቱ ሀገራት የወታደራዊ ደህንነቶች መረጃ ልውውጥ፣ ድንበር ላይ የሚደረጉ ህገ-ወጥ የሰዎች እና የጦር መሳሪያ ዝውውር በጋራ መግታት፣ ወታደራዊ ዲፕሎማሲን ለማጠናከር፣ በተለያዩ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች፣ በትምህርት እና ስልጠናዎች በመደጋገፍ በጋራ መስራት እንደሚገኝበት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት መረጃ አመልክቷል።