በአዲስ አበባ ከተማ 14 ወረዳዎች በስማርት ወረዳነት ተደራጁ

መጋቢት 3/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ ከተማ 14 ወረዳዎች በስማርት ወረዳነት መደራጀታቸውን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ አስታወቁ።

በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ወደ ስማርት ወረዳነት መለወጡን ተከትሎ የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
ወረዳው በቴክኖሎጂ የተሳሰረና ለሕዝቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋ የሚያደርጉ ግብዓቶች እንደተሟላሉለት ተገልጿል።
አገልግሎት ፈላጊዎች ወረፋ የሚጠብቁበት፣ አገልግሎት የሚያገኙበትና የሚስተናገዱበት በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ ሥርዓትም ተሟልቶለታል።

ተገልጋዩ ባለበት ቦታ ሆኖ በበይነ መረብ አገልግሎት የሚያገኝበት አሰራር የሚከተል በመሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቀነስ በኩል ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ እንደገለጹት ከተማ አስተዳደሩ 121 ወረዳዎችን ወደ ስማርት ወረዳነት ለመቀየር ፕሮጀክት ነድፏል።

እስካሁንም 14 ወረዳዎች የላቀ አገልግሎት እንዲሰጡ ወደ ስማርት ወረዳነት መቀየራቸውን ገልፀዋል።

አገልግሎት አሰጣጥን ዘመናዊ ማድረግ ብቻውን ግብ አይደለም ያሉት አቶ ዣንጥራር፤ “አገልግሎት ሰጪው የተለወጠ አስተሳሰብ፣ ሕዝብን እኩል ማስተናገድ የሚችል አዕምሮና ቅንነት መላበስ ይገባዋል” ብለዋል።

የሕዝቡን እርካታ የሚያመጡ ፕሮጀክቶች በቀጣይነት እንደሚተገበሩ ጠቁመው “መዳረሻችንን ብልጽግና አድርገን ወደፊት እንጓዛለን” ሲሉ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ ሉሌ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የሚተገበረው ከከተማዋ እድገትና ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም አገልግሎት መስጠት ግዴታ በመሆኑ ነው ይላሉ።

በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ጊዜና ጉልበት ለመቆጠብና ተደራሽነትን ለማሳደግ የሚጠቅመው ፕሮጀክት በሁሉም ወረዳዎች እንደሚዘረጋ ገልጸዋል።

ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ቢሮው በዚህ ዓመት ከ93 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በአምስት ወረዳዎች ስማርት አገልግሎት ማስጀመሩንም አስታውቀዋል።